ለኩላሊታችን መልካም ጤንነት ስንል ከእነዚህ ልማዶች ብንርቅስ

ኩላሊት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ደም በማጣራት በሰውነታችን ውስጥ የማያስፈልጉ ነገሮችን በሽንት መልክ ማስወገድ አንዱ ነው።በሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀመ አላስፈላጊ ውሃን ማስወገድ እና የካልሺየምና የፎስፌት ማዕድናት መጠንን መቆጣጠርም ሌላኛው ስራው ነው።

የደም ዝውውርን የሚያፋጥኑና የቀይ ደም ህዋስ መመረት ሂደትን የሚጨምሩ ሆርሞኖችንም ያመርታል።

በርካታ ተግባራት የሚከውነው ኩላሊት ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥልና ስራውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውን ታዲያ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ነገሮች መራቅ ይገባል።

የሽንት ቀለም መቀየር፣ ማስመለስ፣ የአተነፋፈስ መዛባት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም እና የመሳሰሉት የኩላሊት በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ይመከራል።

1. ሽንትን ይዞ መቆየት

ሽንት ሳይወገድ በፊኛ ለረዥም ጊዜ ከቆየ ለቫክቴሪያዎች መፈጠር ምክንያት የሚሆን ሲሆን፥ ይህም የሽንት ወይም የኩላሊት ኢንፌክሽን ይፈጥራል።

ስለሆነም በስራ ውጥረትም ይሁን ሌላ የተፈጥሮ ጥያቄን መልስ የሚያዘገዩ ከሆነ ለኩላሊትዎ ሲሉ ከድርጊትዎ ሊቆጠቡ ይገባል እንላለን።

2. በቂ ውሃ አለመጠጣት

ኩላሊት አላስፈላጊ ነገሮችን ለማስወገድ ተግባሩ በቂ ውሃ ስለሚፈልግ በቀን ውስጥ በቂ ውሃ አለመጠጣትም ለኩላሊት ህመም ይዳርጋል።

ሰውነታችን አስፈላጊውን ያህል ውሃ ካላገኘ ደም ስለሚረጋ ወደ ኩላሊታችን የሚሄደው ደም መጠን ይቀንሳል።

ይህም ኩላሊት ከሰውነታችን የሚያስወግዳቸው መርዘኛ ተህዋሳት በበቂ ሁኔታ እንዳይወገዱ ያሰናክላል ማለት ነው።

ስለሆነም በየቀኑ ከ10 እስከ 12 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ኩላሊትዎ ጤናማ እንዲሆን ያግዛል።

3. ጨው አብዝቶ መመገብ

በተደጋጋሚ ጨው የበዛበት ምግብ መመገብም ለኩላሊት ጤና ፀር ነው ተብሏል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጨውን አብዝቶ መውሰድ በሽንታችን ውስጥ የፕሮቲን መጠን እንዲጨምር በማድረግ ለኩላሊት ህመም ይዳርጋል።

በየቀኑ በአጠቃላይ ከምንወስዳቸው ምግቦች ውስጥ የጨው ድርሻ ከ5 ግራም ባይበልጥ መልካም ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

4.መድሃኒቶችን/ ማስታገሻዎችን አዘውትሮ መውሰድ

ብዙዎቻችን ጉንፋን አልያም ራስ ምታት ሲያመን በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚያጎለብቱ ምግቦችና መጠጦችን ከመውሰድ ይልቅ ኪኒን ስለመዋጥ ነው የምናስበው።

መድሃኒቶች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ኩላሊታችን አልያም ሌላ የሰውነት ክፍላችን ሊጉዱ እንደሚችሉ ይነገራል።

አንዳንድ ጥናቶች ማስታገሻዎችን በተደጋጋሚ መውሰድ ወደ ኩላሊት የሚሄደውን ደም እንቅስቃሴ ሊቀንሱ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

5.ፕሮቲን የበዛባቸው ምግቦች

ፕሮቲን ለጤና ጠቃሚ ቢሆንም፥ ቀይ ስጋና የፕሮቲን መጠናቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን በተደጋጋሚ መውሰድ ለኩላሊት በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል።

6. አልኮል

የአልኮል መጠጦችን አብዝተን በምንጠጣበት ወቅት ዩሪክ አሲድ በኩላሊታችን ቱቦ ይከማቻል። ይህም ኩላሊታችን የተለመደ ተግባሩን እንዳያከናውን እክል ይፈጥራል።

ስለሆነም ሁሉም በልኩ ነውና በመጠጡም ለጤናዎ ይወቁበት።

7. ሲጋራ

ሲጋራ ማጨስ በሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች የሚያደርሰው አስከፊ ጉዳት አጠያያቂ ባይሆንም ለኩላሊት ህመም እንደሚያጋልጥም ይነገራል።

ሲጋራ እድሜ እየገፋ ሲመጣ ለሚከሰተው የኩላሊት ህመም መንስኤ ከመሆኑም ባሻገር የኩላሊት ህመምተኞች አጫሾች ከሆኑ ደግሞ በሽታው እጅግ እንዲባባስ እንደሚያደርግ በጥናት ተረጋግጧል።

8. ቡና (ኮፌይን አብዝቶ መጠቀም)

ካፌይን አብዝቶ መጠቀም ለደም ግፊት ከመዳረጉም ባለፈ ኩላሊትንም ይጎዳል።

ካፌይንን ካለ ልክ መውሰድ ለኩላሊት ጠጠር መፈጠር ምክንያት የሚሆን ሲሆን፥ የካልሺየም ንጥረ ነገር ከሽንት ጋር በብዛት እንዲወገድም ያደርጋል።

9.ጉንፋንን የመሳሰሉ ህመሞችን ቸል ማለት

እንደ ጉንፋን፣ ቶንሲል፣ ኢንፍሊዮንዛ ያሉ ህመሞችን በቸልታ ማለፍ ኩላሊትን ሊጎዱ እንደሚችሉ ይነገራል።

እነዚህ ቀላልና የተለመዱ ህመሞችን የሚያመጡ ቫክቴሪያዎችና ቫይረሶች አስፈላጊው ህክምና በወቅቱ ካልተደረገ ኩላሊትን የመጉዳት አቅም አላቸው።

10. እንቅልፍ ማጣት

በተጣበበ ጊዜና የስራ ሁኔታ የሚኖሩ ሰዎች እንቅልፍ የሚያስገኘውን የጤና በረከት ይዘነጉታል።

በእንቅልፍ ስዓት የአዳዲስ ህዋሳት አሮጌዎቹን የመተካት ተግባር ይከናወናል።

በአንፃሩ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት እንደ ኩላሊት ያሉ ሌሎች የሰውነት አካላት ተግባራቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዳያከናውኑ ያደርጋል።

በተጨማሪም በቂ እረፍት ወይም እንቅልፍ አለመኖር ለደም ግፊት ይዳርጋል።

4 thoughts on “ለኩላሊታችን መልካም ጤንነት ስንል ከእነዚህ ልማዶች ብንርቅስ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *