ማይግሬን ወይም ከፍተኛ የእራስ ምታት እና መፍትሄወች

ማይግሬን

ማይግሬን የአዕምሮ መቃወስ ችግር ሲሆን ከፍተኛ በሆነ እና በድግግሞሽ በሚከሰት የራስ ምታት የታጀበ ነው። በርግት ከራስ ምታት ጋር የጠበቀ ተዛምዶ ያለው ቢሆንም ከራስ ምታት በጣም ይለያል። ከራስ ምታቱ በተጨማሪም ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ እንዲሁም ለብርሀን እና ድምጽ በጣም ሴንሴቲቭ መሆንን የመሳሰሉ ምልክቶች አሉት። ማይግሬን በተነሳ ጊዜ ከሰዓታት እስከ ሶስት ቀናት ድረስ ሊቆይ ይችላል። ህመሙ በተከሰተ ጊዜ የሚደረጉ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ሊያባብሱት ይችላሉ። ነገር ግን በየጊዜው የሚደረግ መደበኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድን ማዳበር ወደፊት በሽታው በሚከሰት ጊዜ ለመቋቋም ይጠቅማል።

በታሪክ መዛግብት ስለ ማይግሬን ተጽፎ የሚገኘው የመጀመሪያ ጽሁፍ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1500 አመታት ገደማ በጥንታዊ ግብጽ ሲሆን የህክምና አባት በመባል የሚታወቀው ሂፓክራተስም በ200 አመተ አለም አካባቢ ስለ ማይግሬን እና ምልክቶቹ ጽፎ ነበር።

Sponsored

አንዳንድ ሰዎች ማይግሬይን ከፍሎ በቀኝ ወይም በግራ በኩል ብቻ ሲያማቸው በአንጻሩ ደግሞ አንዳንዶች በሁለቱም በኩል የህመም ስሜት ይሰማቸዋል። በሁለቱም በኩል ያለውን የህመም ስሜት የህክምና ባለሙያዎች ባይላተራል (bilateral) በሚል ስያሜ ይጠሩታል። ከዚህ በተጨማሪም የበሽታው የቆይታ ጊዜ፣ የህመም ስሜት እና የድግግሞሹ መጠን ከሰው ሰው ይለያያል።

ደረጃዎች

ማይግሬን በዋናነት አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነርሱም የመጀመሪያው እና በሽታው ከመቀስቀሱ በፊት ያለው ፕሮድሮም (prodrome) ሲባል ከእሱ በመቀጠል አውራ (aura) ከዚያም በሶስተኛ ደረጃ ዋናው የህመሙ ጊዜ (pain phase) በመጨረሻም ድህረ ህመም (postdrome) በመባል ይታወቃሉ።

የመጀመሪያው ፕሮድሮም ደረጃ ማይግሬይን ከመነሳቱ ከሁለት ቀናት እስከ ሁለት ሰዓታት በፊታ ያለው ጊዜ ሲሆን በዚህ ደረጃ ላይ የስሜት መለዋወጥ፣ ጭንቀት ፣ የጡንቻ መወጠር በተለይም አንገት አካባቢ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት አለው።

ሁለተኛው ደረጃ የሆነው አውራ (aura) ሁሉም ሰዎች ላይ ላይታይ ይችላል። ከሌሎች የህመሙ ደረጃዎችም አጭሩ ሲሆን ከ 5 እስከ 60 ደቂቃ ያህል ብቻ ይቆያል። ይህን ስሜት የሚታይባቸው ሰዎች የስሜት ህዋሶቻቸው በተለይም አይናቸው ችግር ያጋትመዋል ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ነገሮችን ሲያዩ ብዥ ያለ እይታ ያጋጥማቸዋል። መስመር የሌለውም ነገር ላይ ትልልቅ መስመር ይታያቸዋል። በተጨማሪም በዙሪያቸው ያሉ ነገሮች ሲንቀሳቀሱ ያያሉ በእውነቱ ግን እነዚያ ነገሮች ከቦታቸው አልተንቀሳቀሱም።

አንዳንድ ሰዎች የአውራ ደረጃ ሳያጋትማቸው ከመጀመሪያው ደረጃ በቀጥታ ወደ ሶስተኛው ይሄዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ሁለተኛው የህመም ደረጃን ሳያጋጥማቸው ሚያልፉ ሰዎች ዋናው የህመም ስሜት በተቀሰቀሰ ጊዜ በቀኝም በግራ በኩል ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት ስሜትን ያስተናግዳሉ። ሁለተኛውን ደረጃ ያለፉም ሆነ ያጋጠማቸው ሰዎች ወደ ሶስተኛው ደረጃ ሲደርሱ ወደ ዋናው የህመም ደረጃ ይገባሉ። ይህም ከፍተኛ የሆነ እና እጅግ የሚረብሽ የራስ ምታት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ድምጽ፣ ብርሀን እና ሽታ በእጅጉ ይረብሻቸዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጨለም ያለ ክፍል ውስጥ ቢቀመጡ እና በተቻለ መጠን ራሳቸውን ከድምጽ እንዲጠብቁ ይመከራል። በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ ድካም፣ አንገት አካባቢ ላይ የህመም ስሜት፣ ግራ መጋባት ፣ የተዛባ እይታ፣ ጭንቀት እና መሰል ነገሮች ያጋጥማቸዋል።

የመጨረሻው ደረጃ የሆነው ፖስትድሮም (postdrome) አስቸጋሪ የሆነው የህመም ስሜት ቀለል ካለ በኋላ ያለው ጊዜ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት ፣ የባህሪ መለዋወጥ እና የሀንጎቨር አይነት ስሜት ይንጸባረቅበታል።

Sponsored

መንስኤዎች

እስከዛሬ ድረስ የማይግሬን መነሻ ምክኒያት በትክክል አይታወቅም። ነገር ግን ከአንዳንድ አካባቢያዊ ነገሮች ጋር ሊዛመድ እንደሚችል ይታመናል። ወደ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የማይግሬን ኬዝ ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በዘር ሊተላለፍ እንደሚችል ያመላክታል።

ስለመነሻው በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ማይግሬንን የሚቀሰቅሱ አንዳንድ ሁነቶች አሉ ከእነሱም መካከል የእንቅልፍ መዛባት፣ ረሀብ፣ ጭንቀት፣ የአልኮል መጠጥ ፣ የአየር ንብረት እንዲሁም አንዳንድ የምግብ አይነቶች ይገኙበታል። የማይግሬን በሽታ ያለበት ሰው በሽታውን የሚቀሰቅስበትን ምክኒያት ለይቶ ማወቅ እጅግ በጣም ያስፈልገዋል። ቀስቃሽ ምክኒያቶቹን ካወቀ ወደፊት በሽታው እንዳይቀሰቀስ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ ይችላል።

ህክምና

የማይግሬን መነሻ ምክኒያት በትክክል ስለማይታወቅ ፈዋሽ የሆነ መድሀኒትም ሊሰራለት አይችልም። ነገር ግን አስቀድሞ ጥንቃቄ በማድረግ እንዳይከሰት የተቻለውን ሁሉ ማድረግ እና በተከሰተም ጊዜ ህመሙን ለመቀነስ መሞከር ጥሩ አማራጮች ይሆናሉ።

ማይግሬን ያለባቸው ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ ሊያደርጉት የሚገባው ነገር ለራሳቸው ትኩረት ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ መውሰድ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እና በተቻለ መጠን ራሳቸውን ከጭንቀት ማራቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከብርሀን ፣ ድምጽ እና ሽታ ራስን ማግለል አይነተኛ አማራጭ ነው። ህመሙንም ለማስታገስ እንደ አይቦፕሮፊን (ibuprofen) ያሉ መድሀኒቶችን መውሰድ ይመከራል። ህመሙ ለውጥ ካላሳየ እና ከሁለት ቀናት በላይ ከቆየ ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ አስፈላጊዉን የህክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ከዚህ በፊት የህክምና እርዳታ ያገኙ ሰዎች እዚያው በቤታቸው ሆነው ራሳቸውን መንከባከብ እና ማገገም ይችላሉ።

ማይግሬን ያለባቸው ቤተሰቦች እና ጓደኞች ካሏችሁ ይህንን ቪዲዮ አጋሯቸው። ስለተከታተላችሁን እናመሰኛለን።

Sponsored

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *