እስቲ በዙሪያችሁ ያሉ የተለያዩ ህንጻዎችን፣ መኪናዎችን እና መገልገያ መሳሪያዎችን ለማጤን ሞክሩ። በእርግጠኝነት ተፈጥሮአዊ ከሆኑ ነገሮች ውጭ ያሉ በዙሪያችሁ ያሉ ነገሮች ልብሳችሁን ጨምሮ በብዛት ጥቁር ፣ ነጭ ወይም ብረታማ ቀለም ያላቸው ናቸው። ምናልባትም ጊዜን ወደ ኋላ ተጉዘን ለመመልከት ብንችል እና የዛሬ 300 ወይም 400 አመታት ብንመለስ አካባቢያችሁን ከአሁኑ በተሻለ በቀለማት አሸብርቆ እናገኘዋለን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ቀለማት ከምድረ ገጽ ቀስ በቀስ እየጠፉ ነው። ለዚህም ምክኒያቱ የአየር መበከል ወይም የተፈጥሮ አደጋ አይደለም። ይልቁንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሰው ልጆች ቀለማትን ከመጠቀም ራሳቸውን እየቆጠቡ ይገኛሉ።
በጥንት የሰው ልጅ ስልጣኔ ታላላቅ ከተሞች በህብር ቀለማት የተዋቡ እና ያሸበረቁ ነበር። እያንዳንዱ ከተማም ሲገባ የራሱ የሆነ መታወቂያ መልክ ያለው እስኪመስል ድረስ የራሱ የሆነ የሕንጻ ኪነ ጥበብ እና የቀለም አጠቃቀም ነበረው። ወደ አሁኑ ዘመን ስልጡን ከተሞች ስንመጣ ግን ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ አንድ አይነት የህንጻ አሰራር እና ቀለም እየመጡ ነው። በሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች እየተሞሉ ለህንጻዎቻቸውም ግራጫ እና ብረት ቀለማትን ይመርጣሉ። በጥንት እና በአሁን ዘመን ያለው ልዩነት እጅግ ግልጽ ነው። አድዲስ በማደግ ላይ ያሉ የላቲን አሜሪካ እና የአፍሪካ ከተሞችም የራሳችቸውን ጥንታዊ ስልጣኔ እና የአባቶቻቸውን ፈለግ በመተው የምዕራባዊያንና የዱባይን መልክ ለማምጣት ሲሯሯጡ ይግኛሉ።
ወደ ድርጅቶችም ስንመጣ በፊት ከነበራቸው በቀለማት የተዋበ ሎጎ ይልቅ ጥቁር ወይም ግራጫ የሆነ ቀለምን ምርጫቸው እያደረጉ ነው። ከእነዚህም መካከል አይ.ቢ.ኤም (IBM) እና Appleን መውሰድ እንችላለን። በርግጥ የአብዛኛዎቹ ድርጅቶች ሎጎ መቀየር ምክኒያት በብዙ ሀገራት ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳደግ እና ቀለማት ከሀገር ሀገር የተለያየ ትርጉም ስለሚሰጣቸው በተቻለ መጠን አብዛኛው ሰው ጋር የሚስማማውን ቀለም ለመምረጥ ከሚል እሳቤ ነው። በፊት በቀይ እና ቢጫ ቀለማት ይዋብ የነበረው የማክዶናልድስ (MacDonald’s Burger) በርገርም ሱቆቹ አሁን በጥቁር ተተክተዋል። በግለሰብ ደረጃም ብንመለከት የሰዎች የግል መኪኖች ቀለማት በብዛት ግራጫ እና ጥቁር ናቸው። ከዚህ አለፍ ሲልም ነጭ ናቸው። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ተነስተን አለም ከህብር ቀለማት ወደ ነጭ እና ጥቁርነት እየሄደች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ታዲያ ቀለማት ቢጠፉ ይህንን ያህል ሊያሳስበን ይገባል?
ከምታስቡት በላይ ቀለማት ለእኛ ሰው ልጆች እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው። ቀላል ከሚመስለው ጥቅማቸው ብንነሳ ቀለማት የሰውን ስሜት የመቀየር ትልቅ አቅም አላቸው። የተጨነቁ ሰዎች የደስታ ስሜትን የሚፈጥሩ ቀለማትን ሊያገኙ የሚችሉበት እድል ሲፈጠርላቸው ከጭንቀታቸው ቀስ በቀስ ለመልቀቅ ይችላሉ። ለዚህም ምክኒያቱ ቀለማት የደስታ ስሜትን የሚፈጥረው ዶፓሚን (Dopamine) የተሰኘ ሆርሞን እንዲለቀቅ ወደ ሰውነታችን ስለሚያደርጉ ነው። እንደ ሰማያዊ እና ነጭ ያሉ እርጋታን እና ሰላምን የሚሰጡ ቀለማት ደግሞ ሰዎች ከድካም ስሜታቸው እረፍት እንዲያገኙ እና የሰላም እንቅልፍ እንዲተኙ ለማድረግ ትልቅ ሚና አላቸው።
ከዚህ ባለፈ ቀለማት ሰዎች ባህላቸውን እና ማንነታቸውን የሚገልጹባቸው መንገዶች ናቸው። ለምሳሌ ለፈረንሳይ ህዝቦች ከfrench revolution ወዲህ መታወቂያቸው ለሆነ እና እንሞትለታለን ለሚሉት አቋማቸው “ነጻነት ፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት” ወይም እነሱ እንደሚሉት “ሊበሪቴ ፣ ኢጋሊቴ፣ ፍራተርኒቴ” (Liberté, égalité, fraternité) መለያ የሚሆኑ ሰማያዊ ነጭ እና ቀይ ቀለማትን ይወዳሉ። በሰንደቅ አላማቸው፣ በቤታቸው እና ዋና ዋና መንገዳቸው ላይ ይጠቀሙታል።
በአፍሪካ ሀገራት ዘንድም የአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ትልቅ ትርጉም አላቸው። የነጻነት እና የቅኝ አገዛዝ ተቃውሞ ምልክት ናቸው። ከዚህ ባለፈም ለተለያዩ ቤተ እምነቶችን እና የሀይማኖት ተቋማት ቀለማት የተለያየ ትርጉም እና ቦታ አላቸው። ከዚህ የተነሳ ቀለማት ከሰው ልጆች ባህል እና ማንነት ጋር የተቆራኘ ህብረት እንዳላቸው ግልጽ ነው።
የተለያዩ የጥንት ጽሁፎች እና ታሪኮች እንደሚያመላክቱት በተለይም ከክርስቶስ ልደት 2000 አመታት በፊት በጥንታዊ ግብጽ እና ቻይና ቀለማት ለህክምና ይውሉ ነበር። በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እንደ አርት ቴራፒ (Art Therapy) እና ክሮሞቴራፒ (Chromotherapy )ያሉ ህክምናዎች በጭንቀት ውስጥ ላሉ ህሙማን ቀለማትን በመስጠት እንዲስሉ፣ እንዲቀቡ እና ከቀለማት ጋር እንዲጫወቱ በማድረግ ሰዎችን ከተለያዩ የአዕምሮ ጭንቀቶች ፋታ እንዲያገኙ ለማድረግ ያገለግላሉ።
ቀለማት ስለነገሮች ያለንን እይታ በጣም ይለውጣሉ። እቃዎችን የመለየታችንን ሁኔታ ላይም ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ለምሳሌ ኮካ የሚባለው ስም ሲጠራ ቶሎ ብሎ ወደ አዕምሯችን ቀይ ቀለም ይመጣል። ከዚህም በመነሳት ቀለማት አንድን ብራንድ እንድንለይ በማድረግ በንግዶች ላይ ትልቅ አሻራ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪም በምንገዛው ልብስ እና በምንበላው ምግብ ቀላል የማይባል ድርሻ አላቸው።
እንደ ቀይ ያሉ ቀለማት ደንበኞች የምግብ ፍላጎታቸው ከፍ እንዲል በማድረግ ቶሎ ቶሎ እንዲመገቡ ያደርጋሉ። ቀይ ቀለማት ለረዥም ጊዜ ሲቆዩ እረፍት ስለሚነሱ ደንበኞች የሚፈልጉትን ተመግበው ለሌሎች ደንበኞች ቦታ ይለቃሉ። ይሄ በሬስቶራንቶች እና በተለይም እንደ ፋስት ፉድ አይነት አገልግሎት በሚሰጡ ምግብ ቤቶች ዘንድ ይዘወተራል። እንደምሳሌም ፒዛ ሀት እና ኢንጆይ በርገርን ማየት በቂ ነው። ታላላቅ የሆኑ ሆቴሎች ደግሞ በመጋረጃ፣ በብረቶች እና በህንጻቸው ላይ ወርቃማ ቀለማትን ይጠቀማሉ ይህም ቅንጡነት እና ሀብትን የሚያሳይ በመሆኑ ሀብታም እና ዝነኛ ሰዎች ያዘወትሯቸዋል።
ከዚህ አለፍ ሲልም ቀለማት ውሳኔዎቻችንን የመለወጥ አቅም አላቸው። አንዳንድ ቀለማት ልክ ስናያቸው በኛ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ ምንም እንኳን እቃው ጥሩ ቢሆንም የቀለሙ ጥሩ አለመሆን ሳንገዛው እንድንቀር ያደርጋል። ወደ አንዳንድ ሱቆች ለመሄድ እግራችን ሲፈጥን አንዳንዶቹን ለማየት እንኳን ያስጠላናል። ይህም የቀለም ውጤት ነው። አንዳንድ ቀለማት ጭንቀትን ሲፈጥሩ የተቀሩቱ የተስፋን እና ሀሴትን መንፈስ ይፈጥራሉ።
ሆኖም ግን ቀለማት በባህሪያቸው መጥፎ ብቻ ወይም ጥሩዎች ብቻ አይደሉም። እንደየአገባባቸው እና አጠቃቀማቸው የተለያየ አንድምታ አላቸው። ለምሳሌ ጥቁር ቀለምን ብንመለከት አንዴ የጨለማ፣ የባዶነት፣ የጭካኔ እና የሀዘን መልዕክት ሲኖራቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ የደስታ (የሰርግ እና የምርቃት) ፣ የመንግስታዊ እና ቢዝነስ ተቋማት መሪዎች ልብስ በመሆን የልህቀት ምልክት ይሆናሉ። ቀይ ቀለምም በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ የቁጣ እና ደም የማፍሰስ ምልክት በአንጻሩ ደግሞ የፍቅር እና የመስዋዕትነት ምልክት በመሆንም ያገለግላል።
እንግዲህ ቀለማት ከህክምና፣ ከንግድ እና ከሰው ልጆች ደስታ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው ካየን ቀለማት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነገሮች መሆናቸው እሙን ነው። ታዲያ ከስልጣኔ ጋር ተያይዞ ሰዎች የቀለማት አጠቃቀማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ቀለም የለሽነት እየሄደ መሆኑ አሳሳቢ ነው። ስለዚህ ቀለማትን በጥበብ ለሰው ልጆች ጥቅም መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው ። ቀለማት ለእናንተ ምን ናቸው? ከቀለማት ሁሉ የምትወዱት ቀለም የትኛው ነው?
ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን።