በማለዳ የመነሳትን ልምድን ማዳበር

ስንት ጊዜ ይሆን ማልደው ለመነሳት አስበው፤ የማንቂያ ደውል(Alarm) ቀጥረው ልክ የማንቂያ ደውሉ ሲጮኽ ዘግተው ለሽ ያሉት? ለምን ይሆን በጠዋት የመነሳትን ልምድ የምንፈልገውን ያህል ያቃተን? እናስባለን ግን አልተገበርነውም ብዙ ጥረናል ግን እንዳሳብነው ያህል አልሆነልንም። ይሄ ነገር የአብዛኛዎቻችንን ጓዳ ያንኳኳ ችግር ነው። ምናልባትም ልምዱን ለማዳበር የተጠቀምነው ልክ አለመሆን ውጤታማ እንዳንሆን ሳያደርግ አይቀርም። በዛሬው ቪዲዮ ይህን አንስተን ውጤታማ የሆኑ መንገዶችን እናነሳለን።

“85 በማለዳ የመነሳት ቁልፎች” ብለን አታካችና ለመተግበር አሰልቺ የሆኑ ዝርዝሮችን ልናቀርብላችሁ አንሻም። ይልቁንም ከእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ልምምዳችን ባህሪያትና አወቃቀር በመነሳት ግልጽ ፣ ቀላልና ሊተገበሩ የሚችሉ መንገዶችን በማንሳት የመፍትሄ ሀሳብ እናቀርባለን እስከመጨረሻው ይከታተሉን።

በመጀመሪያ ማልዶ መነሳት ለምን አስፈለገ? ለዚህ ብዙ ነገሮችን መዘርዘር እንችላለን። “Early to bed, Early to rise , makes a person healthy, wealthy and wise.” እንደሚባለው ጥናቶችም ይህንንኑ ያመላክታሉ። ይኸውም ማልዶ መነሳት ቀናችንን በብሩህ መንፈስ ለመጀመር ፣ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ፣ ቀደም ብለን በመነሳት በምናተርፋት ሰዓት የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ፣ ከራሳችን ጋር ጊዜ ለመውሰድ እና እጅግ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ጥቅሞች አሉት። የጥናቱን ነገር እንተወውና በጠዋት ማልደው ተነስተው በቀኝ አውለኝ ብለው ፣ ቤት ያፈራዉን ቀመስመስ አድርገው ፣ ከተቻለም የአካል እንቅስቃሴ አድርገው ፣ ሻወር ወስደው ፣ ባለዎት ነገር ፏ ብለው የጀመሩት ቀን እና አርፍደው ተነስተው ወደስራዎም ሆነ ትምህርት ወይንም ሌላ ተግባርዎ የሚሰማሩበት ሰዓት ረፍዶ፤ ስለቀኑ አዋዋልዎ እንኳን የማሰቢያ ጊዜ ሳያገኙ፣ ጫማዎትን እያማተሩ ፈልገው በጥድፊያ እየተንደረደሩ የወጡበት ቀን አንድ ነውን?

ታዲያ እንዴት አድርገን ይህንን ልምድ እናዳብር?

በየዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ደጋገመን ከማድረጋችን የተነሳ ልምድ ሆነውን ምንም ሳናስብ ሳንጨነቅባቸው በቅጽበት የምናደርጋቸው ነገሮች እጅግ ብዙ ናቸው። እነዚህን ልማዶችን ያካበትንበትን መንገዶች በማጤን አዳዲስና የምንፈልጋቸውን ልምዶች ገንዘብ ማድረግ እንችላለን። እኛ የሰው ልጆች አስበንበትም ሆነ ሳናስበው እነዚህ የተከተልናቸው መንገዶች ናቸው ዛሬ ላይ ያሉንን ልማዶች የቀረጹት። እነዚህ መንገዶች ተያያዥነት ያላቸውና እርስ በርስ የሚደጋገፉ፤ አንዳቸው ከጎደሉ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት ከባድ ይሆናል። መንገዶቹን እንመልከት።

የመጀመሪያው ደረጃ – ተነሳሽነት

በዚህ ደረጃ አንድን ተግባር ለማድረግ የሚኖረን ጉጉት ወይንም ተነሳሽነት ነው። ይህ ደግሞ ያን የተፈለገውን ተግባር በማድረጋችን የምናገኘውን ውጤት በማየት ነገሩን ለማድረግ እንድንጓጓ ያደርገናል። ለምሳሌ ያህል ብንወስድ አንድ የሲጋራ ሱስ ያለበት ሰው ብንወስድ ልክ የሲጋራ ሽታ ሲሸተው ፣ ሁሌም የሚያጨስበት ሰዓት ሲደርስና ብዙ ጊዜ የሚያጨስበት አካባቢ ሲደርስ የማጨስ ተነሳሽነት በውስጡ ይፈጠራል። ይህም እንዲ ጉጉትና ምኞትን በውስጡ ይፈጥራል። ሁለተኛው ደረጃም ይህኼው ጉጉት ነው።

ሁለተኛው ደረጃ – ጉጉት

አንድ ሰው እንዲሁ ውስጡ ተነሳሽነት ስላለ ብቻ በመጀመሪያው ደረጃ የተገኘው ተነሳሽነት ወደ ትግባር ይለወጥ ዘንድ እንደ ድልድይ ሆኖ የሚረዳን በውስጣችን ጉጉትና ፍላጎት ሲኖር ነው። ይሄ ጉጉት ግን እንዲሁ ተራ መፈለግ አይደለም። ይልቁንም ከፍተኛ የሆነ አንዳንዴም ልንቆጣጠረው የማንችለው እስኪመስለን ድረስ ያለፈቃዳችን የሚሰማን መሻት ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ረሀብ ነው። የረሀብ ስሜት ሲሰማን ቶሎ መብላት ነው የምንፈልገው። አያችሁ አይደል እንዴት ጉጉት ወደ ተግባር እንደሚጋብዝ?

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በበቂ ሁኔታ ጉጉት ከሌለን ወደ ተግባር መሄዱን ከባድ ያደርግብንና በሀሳብ ብቻ እንድንቀር ያደርገናል።

ሶስተኛ ደረጃ – ትግበራ

መነሳሳቱ በቂ የሆነ ጉጉት አግኝቶ አሁን ተግባር ላይ ደርሰናል። ይህ ደረጃ ዋናው የታሰበው ነገር የሚደረግበት ነው። እዚህ ደራጃ ላይ ለመድረስ የተነስሽነታችን መጠንና በአቅማችን ላይ ይወሰናል። ይህን ስንል ማራቶን የመሮጥ ሞራሉና ጉጉቱ ኖሮን ግን ሀያ ሜትርም እንኳን ከሮጥን አመታት ያለፈን ከሆነ ተግባራዊ ማድረጉ ላይ እጅግ ያስቸግረናል። ለዚህም ነው አስቀድመን አንድን ነገር ለማድረግ ስንነሳ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ማየትና አቅማችንን ያገነዘበ ነገር ማቀድ የሚገባን። ትልቅ ህልም መያዙ መልካም እና ተገቢ ቢሆንም እያንዳንዷ ትልቅ ድል ከአንድ እርምጃ ነው የምትነሳው።

በመልካም ተነሳሽነት በበቂ ጉጉት ትግበራ ደረጃ ላይ ካደረስነው ታዲያ ምን ቀረን?

መቼስ እያንዳንዱ ተግባር ውጤት አለው አይደል? ባደረግነው አንድ ነገር በአዕምሮም ይሁን በሌላው አካላችን ፣ የሚታይ ይሁን የማይታይ የሆነ አስደሳች ወይንም አሳዛኝ ውጤት አለው። ውጤቱ አስደሳች ከሆነ ብቻ ነው ደጋግመን የማድረግ ተነሳሽነቱን አግኘተን በጉጉት ድርጊቱን በድጋሚ ልንተገብረው የምንችለው። ይህም የልማድ ኡደት ውስጥ እንድንገባ ይረዳንና ነገሩን በመደጋገም ባህላችን ማድረግ እንችላለን። ይህም አራተኛዉና የመጨረሻው ደረጃ ይኸውም የውጤት ደረጃ ነው። በአንጻሩ ውጤቱ ካላስደሰተን ግን ነገሩን የመድገም ተነሳሽነት እናጣለን። ለዚህም ነው በቃ ከዚህ በኋላ እሮጣለሁ ብለን ሩጫዋ ስታደክመን ወይንም አጠናለሁ ብለን ቁጭ ብለን ነገር ግን በተቀመጥነባት በዚያች ሰዓት ድካምና እንቅልፍ ስለሚጫጫነን ደግመን የማድረግ ተነሳሽነቱን የምናጣው።

እንግዲህ እነዚህ የመነሳሳት ፣ የመጓጓት ፣ የመተግበርና የውጤት ደረጃዎች ናቸው አንድን ልምድ ባህላችን አድርገው እንድናካብተው የሚያደርጉት ካልን እንዚህን ተጠቅመን እንዴት በጠዋት የመነሳት ልምድ እናዳብር?

ጥሩውና ውጤታማ የሚያደርገው አካሄድ በጠዋት እንድንነቃ የሚያነሳሳንን፣ ጉጉታችንን የሚጨምር፣ ተግባራችንን ቀላልና ውጤቱንም አመርቂ በማድረግ በተደጋጋሚ እንድናደርገ ተነሳሽነትን የሚፈጥርልን እንዲሆን የሚረዳንን ሁኔታ መፍጠር ነው።

እነዚህን ሁናቴዎች እንዴት መፍጠር እንችላለን?

  • ተነሳሽነትን መፍጠር በጠዋት እንድንነሳ የሚረዳንን እና መነሳቱ ምጥ እንዳይሆንብን የሚያግዙንን ነገሮች ማመቻቸት፤ ይህም በመጀመሪያ እንዲሁ “በጠዋት መነሳት” ከሚለው አልፈን የምንነሳበትን ሰዓት ይሄ ነው ብሎ መወሰን። የተወሰነ የጊዜ ገደብ ከሌለው በቀርጠኝነት ማድረግ ይከብዳል። ይሄ ነው የተባለ ሰዓት ካለን ግን ተነሳሽነት ከመፍጠር ባለፈ ራሳችንን የምመዝንበት ፣ እቅዳችን ይሳካ አይሳካ የምንገመግምበትን አማራጭ ይፈጥርልናል። ሌላው ተነሳሽነትን የሚፈጥርልን ነገር ምክኒያታዊነት ነው። በጠዋት መነሳት እንዲሁ በጠዋት ለመነሳት ያህል ከሆነ መልሰን ነው የምንተኛው ። ምክኒያቱም አዕምሯችን ምክኒያታዊ መሆን ይፈልጋል። ጥሩ ምክኒያት ደግሞ ካቀረብንለት ተነሳሽነትን ይፈጥርልናል። ለምሳሌ ፦ በጠዋት ተነስቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ እቅድ ማውጣት ፣ መፅሀፍ ማንበብ እነዚህንና የመሳሰሉ ተግባራትን ከጠዋት መነሳት ጋር አገናኝተን ስናቅድ በጠዋት እንድንነሳ እንደ መነሻ ምክኒያት ይሆኑናል።
  • አጓጊ ማድረግ
    በጠዋት መነሳትን የሚናፈቅ ካላደረግነው በጉጉት ለማድረግ እጅጉን ከባድ ይሆንብናል። ስለዚህ አጓጊ ለማድረግ ደግሞ በጠዋት መነሳትን ማድረግ ከምንወደው ነገር ጋር ማቆራኘት እንችላለን። ለዚህ ቆንጆ ማሳያ የሚሆነው ከሰፈራችን ሰዎች ወይም ከቤተሰባችን አባላት ጋር በማለዳ ተነስቶ እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ ከጓደኞቻችን ጋር የሆነ ለቤታችን ቅርብ የሆነ ቦታ በመምረጥ ቦታው ድረስ የፍጥነት እርማጃ በማድረግ መወዳደር ወይንም ገና ጎህ ሳይቀድ በደንብ ማልደን የመነሳት ሀሳብ ከሆነ ያለን ልብ ወለዶችን ማንበብ እና የመሳሰሉ ስናደርጋቸው የሚያስደስቱንን ነገሮች በጠዋት ከመነሳት ጋር ማያያዝ አጓጊ እንዲሆንና ወደ ተግባር መለወጥ የሚችል እንዲሆን ይረዳናል።
  • ተግባሩን ቀላልና ተወዳጅ ማድረግ
    ወደ ተግባር ስንገባ ውስብስብና አሰልቺ እንዳይሆንብን ከትንሽ መጀመር አይነተኛ አካሄድ ነው። ሁሌም ከረፋዱ 3፡00 የምንነቃ ሰዎች ባንድ ጊዜ 10፡00 እንንቃ ብንል ከበድ ስለሚል በአንጻሩ አሁን ካለን የሚሻል ግብን መምረጥ መልካም ነው። ልምድ በማካበት ሂደት ውስጥ ዋናው ነገር ባንዴ ብዙ ማድረግ ሳይሆን ትንሽም ብትሆን አንዷን ነገር በተደጋጋሚ ማድረጉ ነው ወደ ልምድ የሚያመጣው። ስለዚህ አንድ ሊተገበር የሚችል ሰዓት ይመድቡና እሷን በተደጋጋሚ ሳያቋርጡ አስገዳጅ ነገር ካልኖረ በስተቀር ከ አንድ ቀን በላይ ሳያቋርጡ መተግበር ጥሩ ነው።
    በጣም አምሽተን በተኛን ቁጥር በጠዋት መነሳትን ከባድ ስለሚያደርግብን በጊዜ በመተኛት በቀላሉ ለመነሳት ይረዳናል ። ሌላው ከጠዋት መነሳት ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ የምንቸገረው ነገር የማንቂያ ደወል (Alarm) እንኳን ሞልተን ልክ ሲጮኽ አላርሙን አጥፍተን በዚያው በአንሶላችን ሙቀት ተደብቀን ለሽሽ

የምንለው ነገር ነው። ደግሞ የእንቅልፍ ክፋቱ መነሳት እያለብን የምንተኛት እንቅልፍ ከሌላው ጊዜ ሁሉ ትጣፍጣለች። ስለሆነም ከመተኛታችን በፊት የስልካችንን የደውሉን ድምጽ ከፍ አድርገን ስልኩን ራቅ አድርገን ማስቀመጥ ፤ አንድም በእንቅልፍ ልባችን አላርሙን ከማጥፋት ሲቆጥበን ሁለትም ደግሞ ከአልጋችን ወርደን ስልካችን ድረስ መሄድ ግዴታ ስለሚሆንብን እንድንነቃ ይጋብዘናል። በዚያው ብድግ ብሎ ትጥብጥብ ንቅት ለማለት።

ውጤቱን አስደሳች ማድረግ /መሸለም/


እንግዲህ ሶስቱን ደረጃዎች አልፈን ውጤቱ ላይ ደርሰናል። አብዛኛዉን ጊዜ ግን የነገሮች መልካም ውጤት ገጽታ ወዲያ ላይታይ ይችላል። ለዚህም ነው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ያሰበው ተማሪ በአንድ ቀን ጥናት ያን ያህል ለውጥ ስለማያይ ጥናቱን ከነአካቴው የሚተወው። ስለዚህ እኛ ለራሳችን በያንዳንዷ ተግባር ራሳችንንን ብናበረታታ እና ብንሸልም ውጤቱን ተወዳጅ እና ለነገዉም የሚደገምበት ተነሳሽነት ይፈጥርልናል።
ለምሳሌ ያህል በጠዋት ከተነሳን ቡና ብንጠጣ ፣ ሙዚቃ ብናዳምጥ ወይንም በጠዋት በተንሳን ቁጥር አስር አስር ብር ብናስቀምጥና በሚጠራቀመው ብር ለራሳችን አንድ የምንወደውን ነገር ብንገዛበት ቀላል ቢመስልም ከሚሰጠን የውስጥ “የእችላለሁ” ስሜት የተነሳ በዚሁ ተግባራችን እንድንቀጥል ይጠቅመናል።

በመጨረሻም በጠዋት እንድንነቃ የሚያነሳሱንን ሁኔታዎች ፈጥረን ፣ በብዙ ጉጉት ሀሳባችንን መሬት ላይ አውርደን ፣ በመልካም ውጤቱም ረክተን ተሳክቶልን በጠዋት የምንነሳ ከሆንን ታዲያ በዚች ባገኘናት ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን? እንበልና እርስዎ ከዚህ በፊት 2፡00 ከእንቅልፍዎ የሚነቁ ቢሆንና ከዛሬ ጀመረው 11፡00 ላይ ቢነቁ በቀን ተጨማሪ ሶስት ሰዓታት አገኙ ማለት ነው። ይህም በሳምንት ሲሰላ 21 ሰዓታት እንዲሁም በወር 900 ሰዓት እና በአመት 1095 ሰዓት አተረፉ ማለት ነው።

በዚህ ሰዓት ራስዎ ላይ ሰፊ ጊዜ ቢያጠፉ ከአዕምሮ ብስለት ፣ ከመንፈሳዊ እድገት ፣ ከመሪነት ክህሎት፣ ከአካል ብቃት እንዲሁም ከተለያዩ ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶች ልክ እንደ programming , Graphics Design ያሉ ነገሮችን ቢያዳብሩ ፣ አዳዲስ ቋንቋዎችን ቢማሩ ይሄ ሁሉ ትልቅ ማትረፊያ ነው።

ከዛሬው ቪዲዮ መልካም ትምህርት እንዳገኙ ተስፋ እናደርጋለን። የእናንተንም ሀሳብ አካፍሉን። ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *