ቋንቋ አስተሳሰባችንን ይቀይራል?

የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን በተለየ እርስ በርሱ የሚግባባበት ረቂቅ የሆነ ቋንቋ አለው። በርግጥ እንሣትም የሚግባቡት መንገድ አላቸው። ነገር ግን የእነሱ መግባቢያ በጊዜ ሂደት እና በዘመናት ውስጥ ለውጥ እንዲሁም እድገት የሌለው ድምጸት ነው። ላም “ሙኡኡ” ፣ ውሻም “ውውው” ፣ ድመትም “ሚያው ” ከማለት ያለፈ ሰፊ መልዕክት የሚያዝል፣ የሚጻፍ፣ ለሌላ ትውልድ የሚሻገር እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሻሻል አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ የሰው ልጅ ቋንቋ ድምጸቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ የሚታይበት፣ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ፣ ለመረዳትም እጅግ ጥልቅ የሆነ ነው። 

አሁን ላይ ይህንን የምትከታተሉ ሰዎች የምለውን ነገር ለመረዳት የቻላችሁት በቋንቋ ነው። እኔም ሀሳቤን እያስተላለፍኩላችሁ ያለው በቋንቋ ነው። በቋንቋ አማካኝነት ከዚህ በፊት የምታውቁትን ነገር ብቻ ሳይሆን አስባችሁት የማታውቁትን ነገር እንኳን በአዕምሯችሁ እንዲከሰት ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ አንድ አንበሳ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሱፐርማርኬት በመሄድ ሎሊፖፕ ገዝቶ ወጣ። ልክ ይህንን ስላችሁ ከመቅጽበት በሀሳባችሁ አንድ አንበሳ ሲሮጥ ፣ ወደ ሱፐር ማርኬት ሲገባ እና ሎሊፖፕ ገዝቶ ሲወጣ ስላችኋል። እንግዲህ ማንኛውም ጤነኛ የሆነ ሰው ይህንን ይነቱ ክስተት አያስብም። ከዚህ በፊት አንበሳ ሲባል ከነግርማ ሞገሱ በጫካ ውስጥ ጎምለል ጎምለል ሲል እንጂ በሰፈር መሀል ወደ ሱእር ማርኬት ሲሄድ እና ሎኢፖፕ ሲገዛ ማንም አያስበውም። አሁን ግን ይህንን እያወራሁ ስለሆነ በአዕምሯችሁ ውስጥ ይህ ክስተት ተመስሏል። ይህም የሆነው በቋንቋ አማካኝነት ነው። ታዲያ ከዚህ ተነስተን ቋንቋ አስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ አለው ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

Sponsored

በርግጥ አለም ላይ እጅግ ብዙ አይነት ቋንቋዎች እና የቋንቋ ቤተሰቦች አሉ። በአሁኑ ዘመን ከ5000 እስከ 7000 የሚደርሱ ቋንቋዎች በተለያዩ የአለማችን ክፍል ይነገራል። እና እነዚህ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች የሚያስቡበት መንገድ የተለያየ ነው ማለት እንችላለን? ቋንቋ የሰውን አስተሳሰብ የመቅረጽ አቅም አለው?

ይሄ ጥያቄ ለዘመናት የሰው ልጆች መወያያ ሆኗል። የሮም ኢምፓየር ገዚ የነበረው አጼ ቻርልማኝ ሁለተኛ ቋንቋ መናገር መቻል ሁለተኛ ነፍስ እንደማግኘት ያህል ነው ይል ነበር። ቋንቋ በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ያለው ተጽዕኖ ለረዥም ዘመናት አከራካሪ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ አስርት አመታት ወዲህ ግን በተለያዩ ተመራማሪዎች እና ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ ቋንቋ ከሰው ልጆች አስተሳሰብ ጋር ያለውን ቁርኝት ለማወቅ ተችሏል። 

ቻይናዊያን ህጻናት በፍጥነት ቁጥሮችን መማር ሲችሉ እንግሊዘኛ ተናግሪ ህጻናት ደግሞ ቁጥሮችን ለመማር ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድባቸዋል ለዚህም ምክኒያቱ በእንግሊዘኛ ቋንቋ መሰረት ልጆች ከ 1 እስከ 10 ያሉትን ማለትም one up to ten ከቆጠሩ በኋላ 11 ፣ 12 እያሉ ለመቀጠል ልክ እንደ eleven , twelve ያሉ አዳዲስ ቃላትን ለመማር ግድ ስለሚሆንባቸው ነው። በቻይናዊያን የማንዳሪን ቋንቋ ግን አስራ አንድ ለማለት አዲስ ቃላት ሳይሆን የሚማሩት አስር እና አንድን በማጣመር ten one እንደማለት ስለሆነ አዳዲስ ቃላትን ለመማር አይገደዱም። ይህም አዕምሯቸው ቁጥሮችን ለማጥናት ሰፊ ጊዜ ሳይወስድባቸው በቶሎ እንዲረዱ አስችሏቸዋል።

በአውስትራሊያ የሚገኙ ጥንታዊ የሆኑ የኩክ ታዮር ህዝቦችን ብንመለከት ከተቀረው የአለም ህዝብ በስልጣኔ ወደ ሁላ የቀሩ የሚባሉ ቢሆኑም በአቅጣጫ እውቀታቸው ግን እድሜውን በትምህርት ካሳለፈ አድ ምሁር ይበልጣሉ። እነዚህ ህዝቦች ግራ እና ቀኝ የሚሉ ቃላትን አይጠቀሙም። ለሁሉም ነገር አራቱን ዋና ዋና አቅጣጫ ጠቋሚ ቃላት ነው የሚጠቀሙጥ ለሁሉም ነገር ስላችሁ ለሁሉም ነገር። ከሰላምታ ጀምሮ። የአካባቢው ህዝቦች መንገድ ላይ ተገናኝተው ሰላምታ ሲለዋወጡ እንዲህ ባለ መልኩ ነው። በሀበሻ ዘንድ ጤና ይስጥልኝ እንዴት አደርክ እንደሚባለው በታዮር ህዝቦች ሲገናኙ “ወዴት እየሄድክ ነው?” በማለት ሰላምታቸውን ያቀርባሉ። ያኛው ሰውም “ወደ ሰሜን ምዕራብ እየሄድኩ ነው አንተስ ወዴት ነው የምትሄደው?” በማለት ለሰላምታው ምላሽ ይሰጣል። 

እንበል እና አንድ የታዮር ህዝብ እግራችሁ ላይ ጉንዳን ካየ “ወንድሜ በእግርህ ደቡብ ምስራቅ ላይ ጉንዳን አለ ” ይላችኋል። ወይም አብራችሁ ቡና እየጠጣችሁ ጠረጰዛው ላይ ቦታ እንድታስጠጉለት ካፈለገ “እባክሽ ስኒውን ወደ ሰሜን ምስራቅ አስጠጊው” ይላል። በእውነቱ ይሄ አይነቱ አነጋገር በአብዛኞቻችን የተለመደ ስላልሆነ ግራ ሊያጋባን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ግን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው እና ንግግራቸው መሀል እነዚህን ዋና ዋና አቅጠጫ ጠቋሚ ቃላት ስለሚጠቀሙ አዕምሯቸው ሁሌም ቢሆን ከአቅጣጫ አንጻር ንቁ ነው።

Sponsored

እስቲ ራሳችሁን ፈትኑ። አይናችሁን ጨፍኑ እና ሰሜን ምስራቅ በየት በኩል እንደሚገኝ ለመጠቆም ሞክሩ። አብዛኛው ሰው ይህንን ለማድረግ ይቸገራል። ለአውስራሊያዎቹ የታዮር ህዝቦች ግን ይሄ እጅግ ቀላል ነገር ነው። ከዚህም በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው የምንናገረው ቋንቋ አስተሳሰባችን ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳለው ነው። 

እንግዲህ ቋንቋ በሰው አስተሳሰብ ላይ የራሱ የሆነ አሻራ እንዳለው ካመንን ታዲያ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች አስተሳሰባቸው ይለያያል ወይ ለማለት እንችላለን? ለዚህ መልስ የሚሆነን የቋንቋን ባህሪ ጠንቅቆ ማወቅ ነው። ሁሉም ቋንቋዎች የራሳቸው የሆነ ሰዋሰዋዊ ህግ እንዲሁም መዝገበ ቃላት አሏቸው። ከዚህም አልፎ የራሳቸው የሆነ ፊደላት እና ሆሄያት ያላቸው ቋንቋዎችም አሉ። እንደ አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ፍሬንች፣ ስፓኒሽ እና ፖርቹጊዝ ያሉ ቁንቋዎች ከግራ ወደ ቀኝ ሲጻፉ አረብኛ እና እብራይስጥ ደግሞ ከቀኝ ወደ ግራ ይጻፋሉ።

ይሄ የአጻጻፍ ስርዓት በእነዚህ ቁንቋ ተናጋሪዎች መካከል ስለ ጊዜ ያላቸውን እይታ በእጅጉ ይቀርጻል። ለምሳሌ አንድ አማርኛ ተናጋሪ ግለሰብ እና አንድ አረብኛ ተናጋሪ ሰው ጠርተን ለሁለቱም የባራክ ኦባማን ከልጅነት እስከ እድገት ያለውን ፎቶ እንዲደረድሩ ብንሰጣቸው። አማርኛ ተናጋሪው የኦባማን የህጻንነት ፎቶ በግራ በኩል በማድረግ በቅደም ተከተል ይደረድረዋል። ወደ አረብኛ ተናጋሪው ብንሄድ ደግሞ ከእሱ በተቃራኒ የኦባማን የህጻንነት ፎቶ በቀኝ በኩል በማስቀደም ፎቶዎችን ይደረድራል። ከዚህ እንደምንረዳው ለአማርኛ ተናጋሪው ጊዜ ከግራ ወደ ቀኝ ሲሄድ ለአረብኛ ተናጋሪው ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ይሄዳል። 

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ቋንቋዎች ለተለያዩ ስሞች ጾታን ይሰጣሉ። በጀርመንኛ ፀሀይ እንስታይ ጾታ ሲኖራት ጨረቃ ደግሞ ተባዕታይ ነው። ከዚህም የተነሳ አንድ የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪን ስለ ፀሀይ ንገረን ብትሉት ውበቷ፣ አንጸባራቂነቷ እያለ ለሴት የሚውሉ ቃላትን ይጠቀማል። ከዚህ በተቃራኒ ደሞ ራሽያን የሚናገሩ ሰዎች ፀሀይን በተባእታይ ጾታ ስለሚወክሉት ስለጸሀይ ተናገሩ ቢባሉ ግርማ ሞገሱ፣ ድምቀቱ እያሉ ለወንድ የሚውሉ ገላጭ ቃላትን ሲጠቀሙ ታገኟቸዋላችሁ። አንዷን ጸሀይ ራሽያን ተናጋሪ እና ጀርመን ተናጋሪ  በተለያየ መንገድ አዕምሯቸው እንዲስለው ያደረገው ቋንቋቸው ነው።  በአማርኛም ቢሆን መብራት ተባዕታይ ጾታ ስለሚሰጠው መብራት ጠፋ፣ መብራት ሄደ፣ መብራት መጣ ይባላል። በአንጻሩ ደግሞ ውሀ መጣች፣ ውሀ ጠፋች ይባላል። 

ከዚህ ባለፈ ብዙ ብዙ አይነት ምሳሌዎን እያነሳን ቋንቋ በሰው ልጆ አስተሳሰብ ላይ ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ ብዙ ማለት እንችላለን። በጥቅሉ እንደምንረዳው እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ ዘዬ፣ የአነጋገር ስልት፣ የቃላት ቅወቃቀር፣ ሰዋሰዋዊ ህግጋት እና የቃላት አመሰራረት መንገዶ አሉት። እነዚህ ልዩነቶች በውስጣቸው የተለያዩ እምቅ አቅሞችን ይዘዋል። አንዳንዱ የማስታወስ ችሎታን ሲጨምር፣ አንዳንዱ ስለ አቅጣጭዐ ያላንን የእውቀት አድማስ ያሰፋል ። ሌላውም በየበኩሉ የየራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። አለም ላይ ያሉ ቋንቋዎች ብዙነት ደግሞ ከእያንዳንዱ ቋንቋ የሰው ልጅ ሊያገኘው የሚችለውን ትርፍ እና ጥቅም ስናስበው እጅግ ደስ ይላል።

አዳዲስ ቋንቋን ስንማር ከዚህ በፊት የነበረን ሀሳብ የምንገልጽበት አዲስ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን ያገኘነው ነገሮችን የምናይበት አዲስ መነጽርም ጭምር እንጂ።

Sponsored

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *