በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ እንደ ተአምር በሌሎች እንደ ትንግርት በተቀሩት ደግሞ እንደ ትልቅ ሰው ሰራሽ የወደፊቱ የምድር ፈተና ይታያል። አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ። የበሽተኞችን መረጃ ከመመዘን እስከ መድሀኒት መቀመም ፣ ሰዎችን ከማዝናናት ትልልቅ ቀዶ ጥገናዎች እስከ ማካሄድ እንዲሁም በደህንነት ዘርፍ ፣ በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በመዝናኛ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ያልዳሰሰው የሰው ልጅ እንቅስቃሴ የለም። ከምናስበው በላይ ኤአይ አጠገባችን ደጃችን ያንም አልፎ ጓዳችን አልፏል። በርግጥ አንዳንድ ሰው ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ሲነሳ ሮቦቶችን ብቻ ያስባል። ሮቦቶች በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ታግዘው ለተሰሩበት አላማ ይውላሉ ግን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በሮቦቲክስ ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም ዘርፈ ብዙ መስኮችን የሚዳስስ እና በተለያዩ አማራጮች ተግባር ላይ የሚውል ነው። ማንኛውም ስማርት ስልክ ያለው ሰው ቢያንስ የፌስቡክ ፣ የዩትዩብ ወይም የጎግል ብሮዘር ተጠቃሚ ነው። እነዚህን አማራጮች በመጠቀም መረጃ ሰርች ያደረገ፣ ፍሬንድ ሪኩዌስት የላከ፣ ቪዲዮ ያየ ብዙ ሰው ነው። ስልኩን በጣት አሻራ (Finger print) ወይም በፊት መለያ (Face Recognition) የቆለፈውን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው። ይሄ ሁሉ ሰው አወቀውም አላወቀዉም ባንድም በሌላ መንገድ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ተጠቃሚ ነው ማለት ነው።
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሰው ልጆች ህይወት ጋር እየተቆራኘ በብዙ ዘርፎች ውስጥ እየገባ ይገኛል። እጅግ ብዙ መልካም የሆኑ እድሎችን ይዞልን ቢመጣም በአግባቡ ካልተጠቀምነው ደግሞ የሚያስከትለው ችግር እንዳለ ግልጽ ነው። እንግዲህ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን ተፈላጊነት እና ተግባራዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ ልናስቀረው የማንችለው ነገር እንደመሆኑ እሱም እኛ ጋር ሊሰነብት እንደመምጣቱ እሱን እንዴት እንደምናጠና፣ በምን አግባብ ተግባር ላይ እንደምናውለው፣ በምን መልኩ ለሰው ልጆች ጥቅም ብቻ እንዲውል ማድረግ እንደምንችል ማወቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በተለይም እንደኛ ሀገር ባሉ ለማደግ በሚታትሩ የሰው ልጅ ኑሮ፣ የህክምና መሳሪያዎች በውስንነት በሚገኙበት፣ ትምህርት በጥራት ባልተስፋፋበት፣ ግብርናው እጅግ ኋላ ቀር በሆነበት፣ የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጥፍ በሚያድገበት ሀገር እንዲሁም የምግብ ዋስትና ባልተረጋገጠበት ሀገር ያለውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እና የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ለመሰለፍ የተቀረው የአለም ክፍል ዛሬ ላይ ለመድረስ የሄደበትን መንገድ መከተል እጅግ አድካሚ ከመሆኑም በላይ በእሳት የመጫወት ያህል ዘመኑን ያላመዛዘነ ነው የሚሆነው።
ታዲያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምንድን ነው?
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ የአማርኛ አቻ ትርጉሙ ሰው ሰራሽ ክህሎት ማለት ሲሆን በኮምፒውተር ሳይንቲስቶች እና ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ዘንድ ኤአይ በመባል ባጭሩ ይጠራል። ኮምፒውተሮች ከተሰሩበት ጊዜ ጀምሮ አስፈላጊው መረጃ ይሰጣቸው እና እሱን ኮምፒውት በማድረግ አስፈላጊውን ውጤት ያሳያሉ። ምንም እንኳን ፈጣን፣ ተአማኒ፣ ጊዜ ቆጣቢ ቢሆኑም ነገር ግን ለረዥም ጊዜያት ያህል የኪምፒውተሮች ድክመት ተደርጎ የሚቆጠረው የራሳቸው የሆነ ክህሎት ወይም Intelligence የሌላቸው መሆኑ ነበር። አሁን ግን ይሄ ነገር ታሪክ ሆኗል። ስማርት ስልኮች፣ ስማርት ሰዓቶች፣ ስማርት መኪኖች even ስማርት ቤቶች በዙሪያችን አሉ።
የሰው ልጆች በተፈጥሮ የተቸረን ነገሮችን የመገንዘብ፣ የማስተዋል እና ካየነው ነገር የመማር ችሎታ አለን። ይህን ክህሎት ኮምፒውተሮች እንዲኖራቸው ማስቻል ሰው ሰራሽ ክህሎት (Artificial Intelligence) ይባላል። የሰው ሰራሽ ክህሎት ያላቸው ማሽኖች አካባቢያቸውን በመቃኘት የተሰጣቸውን አላማ ለማሳካት እርምጃ ይወስዳሉ።
AI ተግባራዊ የሆነባቸው መስኮች
በንግድ
አንዳንዴ ገርሟችሁ አያውቅም እናንተ ከገዛችሁት እቃ ጋር አብሮ የሚሄድ ምርት ወይም እናንተ በልባችሁ ለመግዛት ስታስቡት የነበረው ነገር ፊታችሁ ላይ አንድ ሲስተም ሲያቀርብላችሁ? ይሄ አስማት ወይም የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም የሰው ሰራሽን ክህሎት በመጠቀም የሚሰራ Recommendation System ነው። በዚህ ሲስተም ኦንላይን ባሉ የመገበያያ አማራጮች ተጠቅማችሁ በምንሸምቱበት ጊዜ ለናንተ የሚሆኑ ምርቶችን ያቀርብላችኋል። ይህም የሚሆነው ከዚህ በፊት ሰርች ያደረጋችኋቸውን ፣ የገዛችኋቸውን እና ፍላጎታችሁን በማጤን እና በማዛመድ ነው። ይሄም ከኋላው የማቲማቲክስ ቀመሮችን እንዲሁም እንደ Collaborative filtering ያሉ የMachine Learning ዘዴዎችን በመጠቀም ተግባር ላይ ይውላል። ይሄ መንገድ ደንበኞች የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ነጋዴዎችም ምርታቸው ወደሚፈልገው ሰው በቶሎ እንዲደርስላቸው እና ብራንዳቸውንም በደንብ ለማስተዋወቅ ይረዳል።
በትምህርት
በርግጥ የትምሀርት መስክ ከጥንት ጀምሮ በሰው ልጆች የተቀረጸ እና እየተተገበረ ያለ ትልቅ መስክ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስም እጁን እያስገባበት ይገኛል። ከመምህራን በኩል ብንመለከት የውጤት አሰጣጥ እና አደማመር ላይ፣ ትምህርት ቤትም ተማሪዎችን ለመመዝገብ፣ ውጤታቸውን ለማቀናጀት፣ የመምህራንን እና ሌሎች ሰረተኞቻቸውን ደሞዝ ለማስላት፣ የትለያዩ ትምህርቶችን ተማሪዎች የትም ቦታ ሆነው ለመከታተል እንዲችሉ ለማድረ እየጠቀመ ይገኛል። ከዚህ ባለፈም እንደ Voice Assistant ያሉ featureሮችን በመጠቀም መምህራን እንኳን ባይኖሩ በእነዚህ ድምጾች በመታገዝ ተማሪዎች በቀላሉ ለማጥናት እንዲችሉ እድልን ፈጥሯል። ትንሽ ከተለመደው ወጣ ያለ እና የሚያስገርም AI በትምህርቱ መስክ ያሳረፈው አሻራ ደግሞ ተማሪዎች ምን ያህል ትምህርት እየተከታተሉ እና እየተረዱት እንደሆነ የሚመዘግብ እና ለመምህራን የሚያሳውቅ ቴክኖሎጂ ነው። ይሄ ቴክኖሎጂ የበለትደገው በቻይናዊያን ሲሆን Xian Jiangnan በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች ራስ ላይ የሚጠልቅ ባንድ በማድረግ ተሞክሮ ነበር። ማን እየተከታተለ እንደሆነ፣ የማን ትኩረት ደግሞ ሌላ ቦታ እንደሆነ ለምምህራንም ጠቁሟል። ይህም መምህራን የተማሪዎቻቸውን ትኩረት ሰብስበው እንዲያስተምሩ እና ወደ ኋላ የሚቀር ተማሪ እንዳይኖር ረድቷል።
በጤና
በጤናው መስክ አንዳንድ በሽታዎች ከመከሰታቸው በፊት ያላቸውን ምልክቶች በማየት ምርማ ለማካሄድ እና ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ በሽታው እንዳያድግ እና ከቁጥጥር እንዳይወጣ ይጠቅማል። በተለይም የካንሰር ሴሎች ሳያድጉ እና ሳይስፋፉ ለመለየት በእጅጉ ይረዳል። በሽታዎችን ከመለየት አልፎ መድሀኒቶችን በመቀመም ሂደት ላይ የሚደረጉ ጥናቶች ትክክለኛ የሆነ ስሌቶችን እንዲያካሂዱ ያግዛል። ከዚህ ባለፈም ውስብስብ የሆኑ እና ረዣዥም ሰዓት የሚወስዱ ቀዶ ጥገናዎችን ያደርጋል። በተለያየ መንገድ የተለያየ የሰውነት ክፍላቸውን ያጡ ሰዎችም እንዳይቸገሩ እቃዎችን በማቅረብ በማገዝ እንዲሁም ደግሞ ለሰዎቹ በመገጠም እንደ እጅ እና እግር በመሆን ያገለግላል።
በግብርና
እንደ Computer Vision ያሉ የAI አገልግሎቶችን በመጠቀም ሰብሎች እና አፈር ላይ ችግር ካለ ለመመርመር እና ለማከም ይጠቅማል። እንዲሁም እየበቀሉ ያሉ አረሞች ካሉ እነሱን ለመለየት ያግዛል። ከዚህ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጦችን አስቀድሞ በመተንበይ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ ካላ ያሳውቃል። አንዳንዴም እንደ አንበጣ መንጋ ያሉ ወረራዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ሰዎች የግድ በቦታው መገኘት ሳይገኝባቸው ጸረ ተባይ ኬሚካሎችን ለመርጨት ይጠቅማል።
በስዕል
ስዕሎች በሰዓሊያን ምናብ ውስጥ ያለውን ንጽረት አለም ወደ ገሀዱ አለም የሚያመጡ ምናልባትም አንዴንዴ ያው ራሱ ሰዓሊው ካልገለጸልን በስተቀረ በራሳችን የማንረዳቸው መልዕክቶች የሚተላለፍባቸው የጥበብ መንገዶች ናቸው። አንዱ የሳለውን ሌላው ሰው እሱኑን አስመስሎ ለመሳል ሊቸገር ይችላል ። አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ግን ከዚህ አልፎ እኛ ያሰብነውን ቃል ብቻ ስንሰጠው እሱ ስዕሉን ፊታችን ላይ በቶሎ ስሎ ማስቀመጥ ጀምሯል። ከዚህ አልፎ ፋሽን ልብሶችንም ዲዛይን ማድረግ ጀምሯል።
በመዝናኛ
በመዝናኛው መስክ የፊልም ስክሪፕቶችን በማዘጋጀት፣ የፎቶ ማቀናበሪያ filterሮችን በማዘጋጀት ፣ የሰዎችን ፊት ወደ ካርቱን በመቀየር እንዲሁም እንነሱን ከሚመስሉ ታዋቂ ሰዎች ጋር በማመሳል ለሰዎች ደስታ እና ተዝናኖትን ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪም በጌሞች ላይ በስፋት ላይ ጥቅም ላይ ይውላል። እንደምሳሌ ያህል ቼዝ ጌምን በኮምፒውተር ለመጫወት ብትፈልጉ ሌላ ተጋጣሚ ሰው ሳያስፈልጋችሁ በሰው ሰራሽ ክህሎት በመታገዝ መጫወት ትችላላችሁ።
በትራንስፖርት
በእግራችንም ይሁን በመኪና ወይም ሌላ የትራንስፖርት አማራጭ በምንጠቀምበት ጊዜ ያለምንም ችግር ያሰብነው ቦታ ለመድረስ እንደ Google map ያሉ አፕሊኬሽኖች የምንሄድበትን አቅጣጫ እና የት እንደደረስን በመጠቆም እንዲሁም የሚቀረንን ርቀት በማስላት ይጠቅማሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሹፌር ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው መሽከርከር የሚችሉ Self- driving መኪናዎች ስራ ላይ ውለው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
እንግዲህ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጋብራዊነቱ እየጨመረ እና አድማሱ እየሰፋ በቀላሉ የግባራዊ ይሆናል ብለን በማንገምታቸው መስኮች ሁሉ ውስጥ እየገባ ስራዎችን እያቀለለ ይገኛል። ዛሬ እኛ የጠቀስንላችሁ ነገሮች እግጅ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እንዴት ተጀመረ
ከ1960ዎቹ በፊት አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ከልብ ወለድ እና ምኞት ያለፈ ነገር አልነበረም። የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ እናት በመባል የምትታወቀው እንግሊዛዊቷ አዳ ወደፊት እንደ ሰው ሰራሽ ክህሎት አይነት የመማር እና የማገናዘብ አቅም ያላቸው ኮምፒውተሮች ሊሰሩ ይችላሉ ብላ እምነቷንንና ተስፋዋን ተናግራ ነበር። ከ1940 ወዲህ የተለያዩ የማቲማቲክስ ፣ ሳይኮሎጂ፣ ፖለቲካል ሳይንስ፣ ኢኮኖሚክስ እና ኢንጂነሪንግ መስኮች ላይ ያሉ ተመራማሪዎች በየጊዜው በሚያደርጓቸው ጥናቶች እርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እውን ለመሆን ችሏል።
ለAI ጥናት በተለይም ደማቅ አሻራ ካሳረፉት ሰዎች መካከል አንዱ አለን ቱሪንግ /Alan Turing/ ነው። የራሱ የሆነ ፈተና በማዘጋጀትም የማሽኖችን አፈጻጸም ለመገምገም ችሏል። ይህ መመዘኛውም Turing test በማባል ይታወቃል። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም አሜሪካዊያን የራሽያን ቋንቋ መረዳት እና መተርጎም የሚችል ማሽን ለመስራት በሚታትሩበት ጊዜ እግረ መንገዳቸውን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እንዲያድግ ትልቅ ስራን ሰርተዋል። ዛሬ ላይ Natural Language Processing /NLP/ በመባል የሚታወቀው የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍም የመጣው ከዚህ ጥናት ነበር። አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ማሽኖች የሰውን ልጆች ቋንቋ መረዳት ፣ ወደ ሌላ ቋንቋ መተርጎም እና እነሱም የሰውን ቋንቋ መናገር ይችላሉ። በርግጥ ሙሉ በሙሉ በሚፈለገው ደረጃ ባይደርስም ነገር ግን ትልቅ እርምጃን ተራምደዋል። ለዚህም እንደምሳሌ የሚሆኑት የGoogle Translate ቋንቋ መተርጎሚያ፣ የAlexa , Cortana እና Siri Voice assistant ይጠቀሳሉ።
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እና የሰው ልጆች ስጋት
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሰሩ ያሉ የሳይንሳዊ ልብወለድ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች ሮቦቶች በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በመታገዝ የሰው ልጆች ላይ ጦርነት ሲከፍቱ እና ሰውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሲነሱ ያሳያሉ። ከዚህ የተነሳ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምንም አይነት እውቀቱ ሳይኖራቸው እንዲሁ በደሀናው ለሳይንሱ ከፍተኛ ስጋት አድሮባቸዋል። ፊልሞቹ ነገሩን አሁን ካለው እውነታ ለጥጠው እና አጋንነው ነው ያቀረቡት። ይሄ ማለት ግን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እንከን አልባ ነው ማለት አይደለም። በሰው ልጆች የተሰራ ነገር እንደመሆኑ የራሱ የሆነ መልካም ገጽታ እና ስጋት አለው። በመጥፎ ሰዎች እጅ ከገባ እና ለመጥፎ አላማ ከዋለ ቀላል የማይባል ጉዳት ያስከትላል።
በቅርብ ጊዜ በGoogle ካምፓኒ የበለጸገ የFace Recognition ቴክኖሎጂ የጥቁር አሜሪካዊያንን ፎቶ የዝንጀሮ ነው በማለቱ ትልቅ ክርክር አስነስቶ ነበር። ለዚህም ምክኒያቱ ደግሞ የቴክኖሎጂው ችግር ሳይሆን ሶፍትዌሩን ያበለጸጉት ሰዎች ለሲስተሙ እንዲማር የሰጡት የሰዎች ፎቶ የነጮችን ብቻ በመሆኑ ነው። ሆን ተብሎ ይሁን አይሁን ሌላ አከራካሪ ጉዳይ ቢሆንም ለማሽኑ እንደሚገባ ብዙ አይነት ዳታዎችን ከሰጠነው ደግሞ በሚገባ ተምሮ የትኛው መልክ የማን እንደ ሆነ መለየት ይችላል። እንደዚህ አይነት በተለይም ዘር እና ቀለም ተኮር መገለል እንዳይከሰት ለማድረግ ትውልደ ኢትዮጲያዊቷ ዶክተር ትምኒት ገብሩን ጨምሮ ብዙ የኮምፒውተር ሳይንቲስቶች Black In AI የሚል ድርጅት አቋቁመው ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
ከዚህ ባለፈም የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ መስፋፋት ብዙ ስራዎችን ሊያስቀር ይችላል። ይህም የብዙ ሰዎችን የስራ እድል ሊዘጋ እንደሚችል ግልጽ ነው። ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምክኒያት ደግሞ ሌሎች ብዙ አይነት የስራ እድሎች ይከፈታሉ። ስለዚህ ዋናው ነገር ዘመኑን አውቆ በወቅቱ ወደእ ሚያዋጣው ዘርፍ መዞር እና አስቀድሞ ያሉትን ስራዎች በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዘመን ነው። ይሄ ያለ እና የንበረ የህይወት ሂደት ነው። ዘመናዊ ትምህርት ቤት ባልነበረበት እና ፊደል መቁጠር የሚችሉ ሰዎች ቁጥር እጅግ ውስን በነበረበት ጊዜ ለሰዎች ደብዳቤ በመጻፍ ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር። አሁን ላይ ዘመናዊ ትምህርት በመስፋፋቱ ያ ስራ አያዋጣም። ስለዚህ የኮምፒውተር የጽህፈት አገልግሎት መስጠት ጥሩ አማራጭ ይሆናል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የግል ኮምፒውተር ያለው ሰው እየበዛ ሲሄድ ደግሞ ይህንን መንገድ ትቶ ሌላ የተሻለ አማራጭ መከተል ግድ ይላል።
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በኢትዮጲያ
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በኢትዮጵያ የኮምፒተር ኢንጂነሪንግ እና ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ውስጥ ተካቶ በዩንቨርሲቲ ደረጃ ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪም ኦንላይን የሚገኙ ትምህርቶችን በመከታተል በግላቸው የእውቀት አድማሳቸውን እያሳደጉ ያሉ ወጣቶች አሉ። በመንግስት ደረጃም ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በዚህ መስክ ላይ ያደረገ የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል በ ዓ.ም ተመርቆ ስራውን ጀምሯል። በቅርቡ የሳውዲ አረቢያ ዜግነት የተሰጣት ሶፊያ የተባለችው ሮቦት ላይም የውስጥ ሲስተሟን በመስራት ተሳትፎ ያደረጉ iCogLabs የሚባል የሶፍትዌር ድርጅትን አቋቁመው እየሰሩ ያሉ ወጣት ኢትዮጲያዊያንም ለሌሎች በዘርፉ መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶች እንደምሳሌ የሚታዩ ናቸው።
አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ለኢትዮጵያ?
ምናልባት አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ በጣም የተራቀቁ ስራዎችን ማድረግ መቻሉ እንደኛ ሀገር ላሉ እንደ ቅንጦት ሊታሰብ ይችላል። ነገር ግን ወደኛ ሀገር አውድ በማምጣት አስፈላጊ እና አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮቻችን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። በርግጥ እንደ ጃፓን ያሉ እድሜያቸው የገፉ ሰዎች በበዙበት ቦታ ሰዎችን ተክቶ የሚሰራ ሮቦት ስራ ላይ ቢያውሉ ምርታማነታቸውን ያሳድጋል። ይህንኑ ቴክኖሎጂ ወደኛ ሀገር ብናመጣው ግን የስራ አጡን ቁጥር በማብዛት ኢኮኖሚያችንን ከዚህ የባሰ ይጎዳዋል። በሀገራችን ሰፊ የሆነ ስራ አጥ ሰው በመኖሩ እና አብሻኛው የህብረተሰባችን ክፍል ወጣት እና ትኩስ ሀይል ያለው በመሆኑ የሰውን ጉልበት ስራ ላይ ማዋል ይሻላል። ነገር ግን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን የእርሻ ስራችንን ብናዘምንበት ከእርሻ የምናገኘውን ገቢ በማሳደግ እና ምርታማነታችንንን በመጨመር የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ስርዓት እንዲሻሻል በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ የተማረ እና ስራ ፈጣሪ ትውልድን ለመቅረጽ ብንጠቀምበት ትልቅ ለውጥን በአጭር ጊዜ ለማስመዝገብ ይጠቅማል። በጤናውም መስክ የሀኪም ቁጥር ለበሽተኞች በማመጣጠንበት የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተግባራዊ ቢደረግ ያለ ጊዜያቸው የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ እና መድሀኒቶችን በቶሎ ለማግኘት ይረዳል። ስለዚህ ትልቁ ቁም ነገር ቴክኖሎጂዉን በምን እና እንዴት ባለ መንገድ እንደምንጠቀመው ማወቅ ነው።
በዚህ ቪዲዮ ስለ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምንነት እና አጀማመር እንዲሁም ጥቅሞቹ እና ስጋቶቹ በወፍ በረር ዳሰሳ አድርገንላችኋል። ወደፊትም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ዶክመንታሪዎችን ይዘን እንቀርባለን። እስከዛው ድረስ ስለ ዘርፉ ያላችሁን እይታ በኮሜንት መስጫው ስር አስቀምጡልን። ቆይታችሁ ከእኛ ጋር ስለነበረ እናመሰግናለን።