.
‘ታይፎይድ እና ታይፈስ ነው አሉኝ እኮ!’ ይህንን አባባል ወይ እርስዎ ብለውታል ወይ የሆነ ሰው ሲል ሰምተዋል። ግን ታይፈስ እና ታይፎይድ እንደው ሁሌ አብረው ሰው የሚይዙት መንትያ ስለሆኑ ነው (የስማቸው የመጀመሪያ ሁለት ፊደሎች መመሳሰላቸው ምናልባት ወንድማማች ወይም አብሮ አደግ ባልንጀራ ቢሆኑ ነው) ወይስ ሌላ ምክንያት አላቸው?ii
.
‘ዛሬ ሰውነቴን እየቆረጣጠመኝ ነው። ያቺ ታይፈስ እና ታይፎይዴ ተነሳች መሠለኝ፤ እስኪ ላብራቶሪ ሄጄ የታይፈስ እና ታይፎይድ ምርመራ ላሰራ’ የሚሉ ሰዎችም አሉ። እንዴ እነዚህ በሽታዎች እንደ vivax ወባ በውስጣችን እየኖሩ ባሻቸው ጊዜ የሚነሱ ጉዶች ናቸው እንዴ?
ይህንን ጽሁፍ ለመግቢያ ያህል በነዚህ ስላቆች የጀመርኩት የዛሬው አላማዬ መዛግብትን አገላብጬ እና የራሴን እዲሁም የስራ ባልደረባዬ የሆኑ ሀኪሞችን ልምድ መሠረት አድርጌ ስለ ታዋቂዎቹ ታይፎይድ እና ታይፈስ ትክክለኛውን መረጃ ለእናንተ የገጻችን ተከታታዮች ማመቅረብ ስለሆነ ነው።
ከስማቸው መመሳሰል እና ሁለቱም ትኩሳት ከማምጣታቸው በስተቀር ሁለቱ በሽታዎች እጅግ የተለያዩ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሁለቱም በአንድ ሰው ላይ የመከሰታቸው እድል እጅግ አናሳ በመሆኑ ለየብቻ እንመለከታቸዋለን።
.
ታይፎይድ (typhoid fever)
====================
ሳልሞኔላ(salmonella) በሚባል ባክቴሪያ የሚመጣ ሲሆን ከሰው ወደ ሠው የሚተላለፈውም
• በበሽታው የተያዘ ሰው በሚፀዳዳበት ጊዜ በሠገራው የሚወጣው ባክቴሪያ ለመጠጥ ወይም ለምግብ ዝግጅት የሚውል ውሃን ሲበክል
• በበሽታው የተያዘ ሰው ከተጸዳዳ በኋላ እጁን በአግባቡ ሳይታጠብ ምግብ ሲያዘጋጅ ነው።
በባክቴሪያው የተበከለውን ውሀ ወይም ምግብ የሚጠቀም ሰው በበሽታው ሊያዝ ይችላል።
.
ምልክቶቹስ
=========
በመጀመሪያ ሳምንት
• እየጨመረ የሚሄድ ሀይለኛ ትኩሳት
• ብርድ ብርድ ማለት እና ማንቀጥቀጥ
• ጠቅላላ ሠውነት የህመም ስሜት፣ ራስ ምታት መገጣጠሚያዎችን መቆረጣጠም
በሁለተኛው ሳምንት
• ሆድ ቁርጠት
• ተቅማጥ
• የሆድ ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ
በሶስተኛው ሳምንት
• የጉበት እና ጣፊያ ማበጥ
• የአንጀት መድማት
• የአንጀት መበሳት(ከፍተኛ የሆነ የሆድ ህመም)
.
ልብ ይበሉ እነዚህ ሁሉ ምልክቶች ሁሌም ይገኛሉ ማለት አይደለም። ከነዚህ መካከል ሁሌ የሚገኘው ትኩሳት ነው። የበሽታው ስም ራሱ ‘typhoid fever’ ‘የታይፎይድ ትኩሳት’ የተባለው ለዚህ ነው። በሙቀት መለኪያ በተደጋጋሚ ተለክቶ ትኩሳት የሌለው ታካሚ በሽታው ታይፎይድ የመሆን እድሉ በጣም ትንሽ ነው። ይህን ስል ደግሞ ሁሉም ትኩሳት ያለው ሰው ታይፎይድ አለበት ማለት አይደለም። የተለያዩ በሀገራቸን እና በሌሎች የ 3ኛው አለም የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ድንገተኛ ትኩሳት አሟቸው ሀኪም ቤት ከሚሄዱ ሰዎች ውስጥ የተረጋገጠ የታይፎይድ በሽታ የተገኘባቸው ከ10% በታች ናቸው። ሌሎቹስ ታዲያ በሽታቸው ምን ሆኖ ተገኘ? አብዛኛዎቹ በቀላል ቫይረሶች(እንደ ኢንፍሉዌንዛ) የሚመጡ እና በራሳቸው በሳምንት ጊዜ ውስጥ የሚድኑ በሽታዎች ሲሆኑ ወባ ያለበት አካባቢ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በወባ የሚጠቁ ይሆናሉ።
.
ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ ስለምን ብዙ ሰው የታይፎይድ በሽተኛ ነህ ይባላል?
.
ይህን ጥያቄ ለመመለስ የታይፎይድ በሽታ በምን ምርመራ ይታወቃል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።
.
አንድ ታካሚ በርግጥ የታይፎይድ በሽታ አለበት የሚባለው ከደም ፣ ከሰገራ ወይንም ከሽንት የሚወሠድ ናሙና በላብራቶሪ ውስጥ ባክቴሪያ ማራቢያ(culture media) ሳህን ላይ ተጨምሮ ሳልሞኔላ የሚባለው ባክቴሪያ አድጎ ሲገኝ ነው። ይህ ምርመራ ግን በየቦታው በቀላሉ የሚገኝ አይደለም።
.
ታዲያ የታይፎይድ ምርመራ እየተባለ በየክሊኒኩ እና በየላብራቶሪው ያለው ምርመራ ምንድነወ?
.
ይህ ‘Widal test’ (ዋይዳል) እየተባለ የሚጠራው ምርመራ ሲሆን ሰውነታቸን ባክቴሪያውን ለመዋጋት የሚያመርታቸውን ፀረ-ባክቴሪያ ኬሚካሎች (antibodies) መኖር አለመኖራቸውን የሚመረምር ነው።
.
ብዙዎቻችን ውስጥ ከዚህ በፊት በሽታ ባያመጣም ትንሽ ሳልሞኔላ ባክቴሪያ ወደ ሰውነታችን ይገባል። በመሆኑም አብዛኞቻችን ውስጥ መጠኑ አነስተኛ የሆነ የፀረ ባክቴሪያ ኬሚካል ይገኛል። በቀላል አማርኛ widal test ብዙዎቻችን ላይ ቢሰራ ፖዘቲቭ ይሆናል። ይህ ማለት ግን የታይፎይድ በሽታ አሁን አለብን ማለት አይደለም። ከዚህም በተቃራኒ ደግሞ ታይፎይድ በሽታ ያለበትን ሰው widal ምርመራው ኔጌቲቭ ሊሆን ይችላል። በዚህ የተነሳ ያደጉት ሀገሮች widal ምርመራን መጠቀም ካቆሙ ቆይተዋል።
.
Widal ምርመራ ሊጠቅም የሚችለው የፀረ-ባክቴሪያ ኬሚካሉን(antibody) መኖር አለመኖሩን ሳይሆን መጠኑን መናገር ሲችል ነው። ትኩሳተ እና ሌሎች ምልክቶች ያለው ሰው ላይ widal ምርመራው መጠኑ ከፍተኛ የሆነ antibody ካሳየ በሽታው ታይፎይድ የመሆን እድሉ ከፍያለ ነው። ፖዘቲቭ ሆኖ መጠኑ አነስተኛ ከሆነ ግን ታይፎይድ አለ ማለት አይቻልም።
.
ታይፎይድ ከ 5-28 ቀን ሊቆይ የሚችል እና በአግባቡ ካልታከመ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል በሽታ ነው። ታክሞ ሲድን ግን ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። የተወሰኑ ሰዎች ግን ከዳኑ በኋላ እስከ 1 አመት ድረስ በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
.
ህክምናው በሀኪም የሚታዘዙ ፀረ ባክቴሪያ መድሀኒቶችን መውሰድ ነው። ነገር ግን በህብረተሰባችን ውስጥ ማንኛውንም ትኩሳት እና የሠውነት መቆረጣጠም widal ምርመራ ሰርቶ ፖዘቲቭ በሚሆንበት ጊዜ ታይፎይድ ነው እያሉ የፀረ ባክቴሪያ መድሀኒቶችን ያለ አግባብ ማዘዝ የተለመደ ሆኗል። በዚህም የተነሳ እውነተኛው የታይፎይድ አምጪ ባክቴሪያ (salmonella) መድሀኒቶቹን በትንሹ እየተላመዳቸው ነው። ይህም በሽታው በትክክል በሚከሰትበት ጊዜ ለማከም አስቸጋሪ ያደርገዋል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ባክቴሪያው መድሀኒቶቹን ሁሉ ተላምዶ ሊታከም የማይችል እና ገዳይ ሊሆን ይችላል።
.
ሀኪሞች እና የጤና ባለሙያዎች ማንኛውንም በሽታ ታይፎይድ ነው ከማለታችን በፊት ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆንን ራሳችንን እንጠይቅ። የምርመራውንም ጉልበት እና ድክመት እንረዳ።
.
ታካሚዎች ለማንኛውም ትኩሳት እና ቁርጥማት በየፋርማሲው እየሄዳችሁ የታይፎይድ መድሀኒት፣ አሞክሳሲሊን፣ ሲፕሮ፣ ሚዝል ስጡን እያላችሁ አትጠይቁ።
ፋርማሲስቶች ፀረ ባክቴሪያ መድሀኒት ስትጠየቁ የሀኪም ማዘዠ ብትጠይቁ እና መድሀኒቱን ዝም ብሎ መውሰድ ያለውን ጉዳት ለደንበኞቻችሁ ብታስረዱ መልካም ነው።
መከላከያ መንገድ
እንደማንኛውም በተበከለ ውሀ እና ምግብ እንደሚተላለፍ በሽታ መከለላከያው
• ከሽንት ቤት ሲወጡ እጅን በሳሙና እና በውሀ መታጠብ
• ፈልቶ የቀዘቀዘ ውሀ መጠቀም
• በደንብ የበሰለ ነገር መመገብ
• ፍራፍሬዎችን አጥቦ እና ልጦ መጠቀም
• ሰላጣ ነገሮችን ቤት ባግባቡ የተዘጋጁ ካልሆኑ አለመጠቀም የመሳሰሉት ናቸው።