የጀርባ አጥንት የ26 አጥንቶች ስብስብ ነው። የጀርባ አጥንት መሃከል የሚገኙ ርብራብ መሰል ክፍሎች የጀርባ አጥንት ዲስኮች ይባላሉ። እነዚህ ዲስኮች የጀርባ አጥንትን ባለበት ደግፈው ይይዛሉ። ሰውነት ከባድ ሃይል ሲያስተናግድ ሃይሉን የሚቋቋሙ ክፍሎች ናቸው። ዲስክ ጠንካራ ሽፋን ያለው ሲሆን በውስጡ ግን ለስላሳ የሆነ ፈሳሽ አለው።
የዲስክ መንሸራተት የሚባለው በዲስክ ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ቀዳዳ ምክንያት የሚፈጠር የውስጥ ፈሳሽ መውጣት ነው። ይህ ወፍራም ፈሳሽ ነርቮችን የሚረብሽ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ ነው። ይህ መረበሽ ከፍተኛ ህመም ሊፈጥር ይችላል።
አንዳንድ ግዜ በእጅ ላይ የመደንዘዝ እና የድካም ስሜት ይፈጠራል። አንዳንድ ሰዎች ላይ ደግሞ በተቃራኒው ምንም ስሜት አይኖረውም። የተንሸራተተው ዲስክ የነካው ነርቭ ከሌለ የህመም ስሜት አይሰማንም።
የዲስክ መንሸራተት ህመም ምልክቶች
የዲስክ መንሸራተት ስለመከሰቱ ምንም እዉቅና ሳይኖርዎ ወይም ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ሳይኖር ችግሩ ሊኖር/ሊከሰት/ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ምንም አይነት የህመም ምልክቶች ሳያሳዩ በምርመራ ወቅት በራጅ ላይ የዲስክ መንሸራተት መኖሩ ሊታወቅ ይችላል፡፡
የዲስክ መንሸራተት በሚኖርበት ወቅት የሚኖሩ የህመም ምልክቶች:-
• የእጅ/የእግር ላይ ህመም፡- የዲስክ መንሸራተቱ ያጋጠመዉ በታችኛዉ የጀርባ አጥንቶች አካባቢ ከሆነ ከፍተኛ ህመም በመቀመጫዎ፣ በጭንዎና በባትዎ አካበቢ እንዲሁም መርገጫዎ/የእግር መዳፉ ላይ ሊሰማዎ ይችላል፡፡ የዲስክ መንሸራተት ያጋጠመዎ አንገትዎ ላይ ከሆነ ህመሙ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማዎ በትከሻና በእጅዎ ላይ ነዉ፡፡ ሕመሙ በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበት ወቅት ወይም ወደ ተወሰነ አቅጣጫ የጀርባ አጥንቶችዎን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት ሊባባስ ይችላል፡፡
• የእጅ/ እግር መስነፍ፡- በዲስክ መንሸራተት ምክንያት የተጎዳ ነርቭ ካለ ያ የተጎዳዉ ነርቭ እንዲሰራ የሚያደርገዉ ጡንቻ ሊደክም ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ መራመድ መቸገር፣እቃ ማንሳት ያለመቻል ወይም መያዝ ያለመቻል ሊከሰት ይችላል፡፡
• የመደንዘዝ ወይም የመጠቅጠቅ ስሜት
• የማቃጠል ስሜት
• የጡንቻ ህመም
• የዲስክ መንሸራተት ምልክቶች ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ በራሳቸው ግዜ ሊጠፉ ይችላሉ።
መንስኤዎች
የዲስክ መንሸራተት ዋነኛ መንስኤ ከጊዜ ጋር የሚፈጠር የጀርባ እንቅስቃሴ ውጤት ነው። ዲስክ ከእድሜ ጋር ውሃማ ይዘቱን ያጣል። ይህ የፈሳሽ መቀነስ በዲስክ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
ለዲስክ መንሸራተት ተጋላጭነት የሚጨምሩ ነገሮች
• እድሜ
• የሰዉነት ክብደት፡- ክብደትዎ ከመጠን በላይ የጨመረ ከሆነ በጀርባ አጥንተትዎና ዲስኩ ላይ ጫና ይፈጥራል፡፡
• የስራዎ ሁኔታ፡- የስራቸዉ ፀባይ ጉልበት የሚጠይቅ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
• በተደጋጋሚ ከባድ ነገር የሚያነሱ፣ የሚጎትቱ፣ የሚገፉ፣ ወደ ጎን መታጠፍና መጠማዘዝ የሚያበዙ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡
• በዘር የሚመጣ፡- አንዳንድ ሰዎች ለመሰል ችግር ተጋላጭነታቸዉ መጨመር በዘር ሊወረስ ይችላል፡፡
• የዲስክ መንሸራተት ህክምና
• የጀርባዎ ህመምዎ ወደ እጅዎና እግርዎ የሚሰራጭ ከሆነ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
የአኗኗር ዘይቤ ለዉጥና የቤት ዉስጥ ህክምና
1. የህመም ማስታገሻ፡- ያለሃኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ እንደ አይቡፕሮፌን/አድቪል/ መዉሰድ
2. ሙቀት/ቀዝቃዛ ነገር መጠቀም፡- በመጀመሪያ ቀዝቃዛ ነገር ቦታዉ ላይ መያዝ ህመሙንና መቆጥቆጡን እንዲቀንስ ይረዳል፡፡ ከተወሰኑ ቀናት በኃላ ሙቅ ነገር መያዝ ምቾትና የህመም ፈዉስ እንዲሰማዎ ስለሚያደርግ በቦታዉ ላይ መያዝ
3. ከመጠን ያለፈ እረፍት ያለማድረግ/ማስወገድ፡- ከመጠን ያለፈ እረፍት የመገጣጠሚያዎች መጠንከር/መተሳሰር እና ጡንቻዎች መስነፍ እንዲመጣ ስለሚያደርግ የፈዉሱን ጊዜ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ይልቁንም በሚመችዎ አቅጣጫ ለ30 ደቂቃዎች እረፍት ማድረግና ከዚያን ለአጭር ጊዜ ወክ ማድረግ አሊያም የተወሰኑ ስራዎችን ማከናወን፡፡
ከህመምዎ እያገገሙ ባሉበት ወቅት ህመሙን ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች/እንቅስቃሴዎች መቆጠብ፡፡
ከዲስክ መንሸራተት እንዴት መከላከል ይቻላል?
• ከፍተኛ የሰውነት ክብደት እንዳይኖርዎ ተጠንቀቁ
• ክብደት ሲያነሱ የሰውነት አቋምን ማስተካከል
• የዲስክ መንሸራተት ምልክቶች ካዩ በቂ እረፍት መውሰድ እና ተገቢውን ህክምና ማከናወን