ግራኝ እጅ መሆንና ተያያዠ እውነታወች

ለመጻፍ፣ ስራ ለመስራት፣ እቃ ለማንሳት አዘውትራችሁ የምትጠቀሙት የትኛውን እጃችሁን ነው? የግራ እጃችሁን ወይስ የቀኝ እጃችሁን? የግራ እጃችሁን ከሆነ ግራኝ ናችሁ ማለት ነው። ግራኝ የሆነ ሰውስ ታውቃላችሁ ? ሰዎች ለምን ግራኝ ወይም ቀኝ ሆነው እንደሚወለዱ ሙሉ በሙሉ የሚያስረዳ የሳይንስ ግኝት እስካሁን ድረስ ባይገኝም ከዘረመል እና ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል አጥኚዎች ይናገራሉ።

ከሳይንሳዊ ጥናቶች ወጣ ስንል ደግሞ በጥንታዊ ስልጣኔዎች እና ባህሎች ግራኝ ከመሆን ጋር ተያይዘው የሚነሱ ብዙ አይነት እሳቤዎች አሉ። በአንዳንድ ባህሎች ግራኝነት እንደመልካም አጋጣሚ ሲታይ በሌሎች ደግሞ እንደመጥፎ ነገር ተደርጎ ይወሰዳል። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የዙሉ ነገዶች ግራኝ መሆን ጥሩ አይደለም ብለው ስለሚያስቡ በጉድጓድ ውስጥ የሞቀ ውሀ በማድረግ ልጃቸው ሙቁን ውሀ በግራ እጁ እንዲነካ ያደርጉታል። በጥንት ህንዳዊያን ዘንድ ደግሞ ከዚህ በተለየ መልኩ ግራኝ የሆኑ ሰዎች ልዩ መንፈሳዊ አቅም እንዳላቸው ስለሚታወቅ በማህበረሰቡ ዘንድ መልካም ተቀባይነት እና ከበሬታ አላቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች ግራኝ የሆነ ሰው ከሌሎች ሰዎች በተሻለ ጥበብ፣ ማስተዋል እና እውቀት አለው ብለው ያምናሉ። ወደ ስኮትላንድ ስንመጣ ደግሞ በስኮትላንዳዊያን ዘንድ ግራኞች ጥሩ የሆነ ቦታ የላቸውም። አንድ ስኮትላንዳዊ መንገደኛ መንገድ ሊጀምር ሲል ግራኝ የሆነ ሰው ካገኘ መጥፎ እድል እንደሚገጥመው ያስባል። በእስያም ሆነ በሀገራችን ደግሞ በግራ እጅ መብላት፣ በግራ እጅ ሰው ሰላም ማለት እና ለሰዎች ነግራ እጅ እቃ መስጠት እንደነውር ይቆጠራል።

ጥንታዊ ግሪካዊያን የልብን የደም ዝውውር በዋናነት የሚቆጣጠረው የደም ስር የሚገኘው በግራ እጅ አራተኛው ጣት ላይ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ከዚህም የተነሳ አንድ አፍቃሪ ቀለበቱን በዚህ ቦታ ሲያስር ከልብ የሆነ ፍቅር እንዳለው እና ልቡም ለዛች ላፈቀራት ሴት ብቻ እንደሚመታ ለማሳየት ቀለበቱን ያስራል። ይህም እስካሁን ድረስ በሰፊው የአለም ማህበረሰብ ዘንድ እየተተገበረ ይገኛል።

እንግዲህ ስለ ባህሎች ይህንን ያህል ካልን በሳይንስ የተረጋገጡ ብዙ እውነታዎች ደግሞ አሉ። የግራ እጃቸውን ለብዙ ስራዎች በዋነኛነት ስለሚጠቀሙ ወይም ግራኝ ስለሆኑ ሰዎች አስደናቂ እና አስገራሚ እውነታዎችን ለማወቅ እስከመጨረሻ ድረስ ተከታተሉን።

ግራኝነት በሽታ ወይም ችግር አይደለም። ከሁለቱ እጆች መካከል አንዱ ዋና (dominant) ሲሆን እና ሁለተኛው አጋዥ (recessive) ይሆናል። ግራ እጃቸውን ከቀኝ እጃቸው በበለጠ ለዋና ዋና ግልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎች ግራኝ ይባላሉ። ከብዙ ጥናቶች ለመረዳት እንደሚቻለው መንታ የሆኑ ሰዎች ግራኝ የመሆን እድላቸው በጣም ሰፊ ነው። በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶችም የሚያመላክቱት ይህንንኑ ነው። ብቸኛ ሆነው ከተወለዱ ሰዎች መንታ የሆኑ ልጆች በአብዛኛው ግራኝ ናቸው። ምናልባትም ይሄ ከዘረመል አቀማመጣቸው ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ግራኝ መሆን በዘር ሊተላለፍ የሚችል ነገር የመሆን እድሉ በጣም ከፍተኛ ነው። አንዲት ግራኝ የሆነች እናት ግራኝ የሆነ ልጅ የመውለድ እድሏ ከፍተኛ ነው። Daily Mail የተባለ የመገናኛ ብዙሀን የእንግሊዟ ንግስት ኤሊዛቤት፣ ልዑል ቻርልስ እና ልዑል ዊሊያም ግራኝ መሆናቸውን ዘግቧል።

ግራኝ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የበለጠ አስተሳሰብ ላይ ብልሆች ወይንም intelligent ናቸው። በተለይም የሂሳብ ስሌት እና አቅጣጫ የመለየት አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ከዚህም የተነሳ ጥሩ የኪነ ህንጻ ባለሙያ ወይም አርክቴክት ቢሆኑ ውጤታማ የመሆን እድል አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ ነገሮችን በመራመር እና በመፈላሰፍ አዳዲስ ነገር የመፍጠር ብቃት አላቸው።

በስፖርት ዘርፍ

ግራኝ ሰዎች ስፖርት ላይ በጣም ጥሩ የሚባል አቅም አላቸው። ቦክስ፣ ቴኒስ፣ ጎልፍ፣ ቤዝ ቦል እና የመሳሰሉት የግላቸው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። Rick Smits “The puzzle of left-handedness” በሚል መጽሀፉ ላይ እንዳመለከተው

ቀኝ የሆኑ ስፖርተኞች በቀኝ እጃቸው ልምምድ አድርገው ግራኝ የሆነ ተቃራኒ ቡድን ሲገጥማቸው በግራ እጃቸው ለማጥቃት በጣም ይቸገራሉ። ግራኝ የሆኑ ስፖርተኞች ግን ምንም እንኳን በግራ እጃቸው ብቻ ልምምድ ቢያደርጉም የግድ በቀኝ እጃቸው ማድረግ ያለባቸው ነገር ሲገጥማቸው ብዙም ሳይቸገሩ ተግባራቸውን ወደ ቀኝ እጃቸው ማምጣት ይችላሉ። በአለማችን ላይ ያሉ ታዋቂ የቴኒስ ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ ግራኝ ናቸው። ለምሳሌ ያህል Rod Lever, Jimmy Connor, Marcelo Rios

እና John Mcenorን መጥቀስ ይቻላል።

የአለም የግራኞች ቀን የሚባል እንዳለ ታውቃላችሁ? የአለም ሴቶች ቀን፣ የህጻናት ቀን፣ የሰራተኞች ቀን እንዲሁም የመምህራን ቀንን የመሳሰሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና መልካም ነገርን የማበረታቻ ቀን እንዳለው ሁሉ የአለም የግራኞች ቀንም ይከበራል። ይሄ ቀን ታስቦ የሚውለውም በየአመቱ ነሀሴ 7 ቀን ላይ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄ ቀን የተከበረው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1976 Dean Campbell የተባለ የአለም ግራኝ ሰዎች ማህበር መስራች በሆነው ሰው ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ ሲከበር ባለፈው የነሀሴ ወር ላይም በአለም ደረጃ ለ45ተኛ ጊዜ ተክብሯል። በዕለቱ ግራኝ የሆኑ ሰዎች ልዩ መሆናቸውኘሚያስቡበት እና እርስ በርስ የሚተዋወቁበት ቀን ነው። እናንተም ግራኝ የሆነ ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ካላችሁ ስጦታ በመስጠት እንደምትወዷቸው እና እንደምታበረታቷቸው ግለጹላቸው።

እንስሳትስ ግራኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ ታውቃላችሁ?

በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንስሳትም ልክ እንደ ሰዎች ግራኝ እና ቀኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ድመቶችን ብንመለከት አብዛኛዎቹ ድመቶች ቀኝ እጃቸውን ሲያስቀድሙ የተወሰኑቱ ደግሞ ምንም ነገር ለማድረግ የግራ እጃቸውን ያስቀድማሉ። ይህም በፐርሰንት ሲሰላ ወደ 40% የሚሆኑ የድመት ዝርያ ያላቸው እንስሳት ግራኝ ሲሆኑ 60 % ደግሞ ቀኝ ናቸው። በውሻዎች የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የውሾች ግራኝ ወይም ቀኝ መሆን እኩል በኩል ነው። ይኸውም 50% ቀኝ 50% ግራኝ ናቸው ማለት ነው።

ከአሜሪካው ብሄራዊ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የሰው ልጆችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጨረቃ ይዛ ከሄደችው የአፖሎ መንኮራኮር ውስጥ ከተሳተፉ እና በምርምር ሂደቱ ትልቅ ሚና ካላቸው የጠፈር ተመራማሪዎች ውስጥ 20% ግራኝ ናቸው።

እስቲ በቤታችሁ ወይም በአካባቢያችሁ ምን ያህል ግራኝ ሰዎችን እንደምታውቁ ለማሰብ ሞክሩ።

አሰባችሁ አይደል? በእርግጠኝነት ግራኝ እንደሆኑ የምታውቋቸው ሰዎች እና ቀኝ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ብታወዳደሩ የቀኝ ሰዎች ቁጥር ብዙ ሲሆን የግራኞቹ ግን ትንሽ ነው። ይሄ እናንተ ጋር ብቻ ያለ ነገር ሳይሆን እንደ አለምም ያለው የግራኝ ሰው ቁጥር ትንሽ ስለሆነ ነው። በአለማችን ላይ ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ 10 % የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ግራኝ እንደሆኑ ይነገራል። ይህም ከተቀረው የአለም እጅግ በጣም በቁጥር በጣም ትንሽ እንደሆኑ ያሳያል።

አዲስ ነገር የመስራት

Chris Magmanus የተባለ የለንደን ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና ተመራማሪ ባጠናው ጥናት እንዳመለከተው ግራኝ የሆኑ ሰዎች በቀኝ በኩል ያለውን የአንጎላቸውን ክፍል አዘውትረው ተግባር ላይ ያውላሉ። ይህም ክፍል ከአዲስ ነገር መፍጠር፣ መመራመር፣

የመፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅ ጋር የተሳሰረ ነው። ከዚህ የተነሳ ግራኝ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አርቆ አሳቢዎች፣ አዲስ ነገር ሞካሪዎች እና መፍትሄ አፍላቂዎች ናቸው። ከዚህም ባለፈ ለብዙ ስራዎች የግራ እጃቸውን የሚያስቀድሙ ሰዎች ለአንድ ችግር ብዙ አይነት መፍትሄዎችን ያስባሉ።

ተጽዕኖ ፈጣሪዎች

ግራኞች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ይሄ አለማችን ላይ ለውጥ ያመጡ፣ የሰው ህይወት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠሩ እና ተወዳጅነትን ያተረፉ ከመሆን አላገዳቸውም። ግራኝ የሆኑ እና ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ብዙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ነበሩ። አሁንም ብዙ አሉ። ከታሪክ ብንነሳ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ እና ሊዮናርዶ ዳቪንቼን መጥቀስ እንችላለን። ከፊልም ተዋኒያን መካከል ጀኒፈር ሎረንስ፣ ቶም ክሩዝ፣ አንጀሊና ጆሊ፣ ሞርጋን ፍሪማንን ማግኘት እንችላለን። በሙዚቃው አለም ሌዲ ጋጋ፣ ጀስቲን ቢበርን ስንጠቅስ በጠፈር ምርምሩ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ያረፈውን ኒል አርምስትሮንግን እናነሳለን። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ዘርፎች ተጽዕኖ ከፈጠሩ መካከል ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ የመጀመሪያ ጥቁር አሜሪካዊው መሪ ባራክ ኦባማ እና ባለሀብቱ ቢልጌትስን ማየት ይቻላል።

ግራኝ ሰዎች በጣም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እንደሆኑ ሁሉ በአለማችን ላይ በጣም ታዋቂ ወንጀለኞች እና ነፍሰ ገዳዮች ግራኝ ናቸው። ኦሳማ ቢን ላደን ፣ ቦስተን ማራቶን ላይ ብዙዎችን የገደለው ወንጀለኛ፣ jack the ripper ፣ john Dinglerን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይሄ ማለት ግን ሁሉም ግራኞች መጥፎ እና ወንጀለኞች ናቸው ማለት አይደለም። በጣም ብዙ በጎ ስራ የሰሩ እና ለአለማችን ትልልቅ ነገር ያበረከቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግራኞችም ነበሩ። እነሱን ወደኋላ ላይ እናነሳለን።

Tip: left hand ወይም ግራ እጅ የሚባል ከተማ አለ። ይህም ከተማ በምዕራባዊ ቨርጂኒያ የሚገኝ ሲሆን ስያሜውን ያገኘውም left hand /ግራ እጅ/ ከሚባል ወንዝ ነው።

የመሪነት ችሎታ

ግራኝ ሰዎች ልዩ የሆነ የመሪነት አቅም አላቸው። በሚማሩበት ክፍል፣ በሚሰሩበት ቦታ፣ በጓደኞቻቸው መሀል የመሪነቱን ሚና አስበውበትም ሆነ ሳይውቁት ሰዎች ሲመሩ እና ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። የአሜሪካ ፕሬዝደንቶችን እንኳን ብናይ James Garfield, Bill Clinton , Ronald Reagan, Harry Truman, Gerald Ford እና ቅድም የተጠቀሰውን ባራክ ኦባማን ማንሳት እንችላለን።

በርግጥ እስካሁን ድረስ በሳይንስ የተረጋገጠ ማስረጃ ባይኖርም ብዙ ሰዎች ግራኞች ከሌላው ሰው የበለጠ የህይወት እድሜ እንደሚኖረው ያምናሉ።

በዚህ ቪዲዮ ከቀረቡት ዝርዝሮች መሀል የትኛው አስደነቃችሁ? ኮሜንት ላይ አስቀምጡልን። የምታውቋቸው ግራኝ የሆኑ ሰዎች ካሉ ደግሞ ይህንን ቪዲዮ ሼር አድርጓቸው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *