አለርጂ ምንድን ነው?
አለርጂ ማለት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘው እና በሽታን ለመከላከል እንዲሁም ለመቋቋም የሚሰራውን Immune systemማችን አንዳንድ ነገሮችን ሴንስ በሚያደርግበት ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ ነው። እነዚህ ነገሮች ያን ያህል ጉዳት የሌላቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ሰውነታችን ግን እንደ ስጋት ከቆጠራቸው እነሱን ለመቃወም የተለያዩ ለውጦችን ያሳያል። እነዚህ ለውጦች ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ የአይን መቅላት፣ በተለያየ የሰውነት ክፍል ላይ ማሳከክ፣ እብጠት፣ ማስነጠስ፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና መቁሰልን ያካትታሉ።
መንስኤዎች
ለአለርጂ መከሰት እጅግ ብዙ አይነት መንሴዎችን ለመዘርዘር ቢቻልም አብዛኛዎቹን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው ከታማሚው ጋር የሚያያዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከአካባቢ ጋር የሚያያዝ ነው። ከታማማዊ ጋር የሚያያዝ ስንል ከዘር፣ ከእድሜ፣ እና ጾታ ጋር የሚያያዙትን ምክኒያቶች ሲሆን ከእነዚህ መካከል በዘር የሚመጣው እንደ ዋነኛ ምክኒያት ይወሰዳል። ሁለተኛው እና ከአካባቢ ጋር የሚያያዝ መንስኤ ደግሞ ከአካባቢ ብክለት፣የአመጋገብ ስርዓት ለውጥ እንዲሁም ገና ትንሽ ልጆች እያለን ካጋጠመን የጤና እክል ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል።
እንደ አጠቃላይ በሁለት ከፍለን አየናቸው እንጂ ብዙ መንስኤዎችን መጥቀስ እንችላለን። ለአለርጂ መነሻ ምክኒያት ከሚሆኑ ነገሮች ውስጥ አቧራ አንዱ ነው። ከአፈር ብናኝ እና አቧራ የሚመጡ አለርጂዎች ከማሳከክ ጀምሮ የአስም በሽታን እስከመቀስቀስ ድረስ ትልቅ ጉዳት ያስከትላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከምግቦች የሚመጣ አለርጂ አንዱ ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ከምግብ የሚመጣ አለርጂ በሌላ ምክኒያት ከሚመጡ አለርጂዎች በእጅጉ ይልቃል። አብዛኛውን ጊዜ ለአለርጂ የሚያጋልጡ ልክ እንደ አኩሪ አተር፣ የላም ወተት፣ ስንዴ፣ ለውዝ እና አሳ ያሉ ምግቦች ናቸው። ከእነዚህ መካከል በጣም በህጻናትም ሆነ በአዋቂዎች ዘንድ አለርጂ በማስከተል የሚታወቀው ለውዝ ነው። ከወተት እና ከወተት ተዋጽኦዎች የሚመጣ አለርጂ ላክቶዝ ኢንቶለራንስ ( Lactose Intolerance) በመባል ይታወቃል። ይህም የሚከሰተው ሰውነታችን በወተት ውስጥ የሚገኘውን ላክቶዝ የተባለ ስኳር መፍጨት እና በአግባቡ ለሰውነታችን ጥቅም ላይ ማዋል ሲያቅተው ነው።
ከምግቦች ባለፈ አንዳንድ መድሀኒቶችም ለአለርጂ ምክኒያት ሊሆኑ ይችላሉ። በተለይም ፐኒሲሊን (Penicillin) የተባለው መድሀኒት ከሚወስዱት ሰዎች ውስጥ 10% የሚሆኑቱ አለርጂ እንዲከሰትባቸው ያደርጋል። እንደ ንብ፣ ጉንዳን እና ትንኝ ያሉ ነፍሳትም በመናከስ ሰዎችን ለአለርጂ ያጋልጣሉ። በተለይም ሲናከሱ ወደ ሰውነት የሚረጩት ኬሚካል ሰውነታአችን በቶሎ እንዲቆጣ ያደርገዋል።
አንዳንድ አለርጂዎች በዘር ይተላለፋሉ። ለምሳሌ ለለውዝ አለርጂክ የሆኑ ወላጆች ለለውዝ አለርጂክ የሆኑ ልጆችን የመውለድ እድላቸው ከፍተኛ ነው። መንታ የሆኑ ልጆችም ተመሳሳይ የሆነ አለርጂ ይኖራቸዋል። መንታ በሆኑ እና ባልሆኑት ላይ የተደረግ ጥናት እንደሚይስረዳው መንታ ያልሆኑ ወንድማማቾች ለተመሳሳይ አለርጂ የመጋለጥ እድላቸው 40% ሲሆን መንታ የሆኑቱ ደግሞ 70 % ያህል የተጋለጡ ናቸው።
አስቀድመው ከተጠቀሱት ምክኒያቶች በተጨማሪ የንጽህና ጉድለት፣ ጭንቀት ፣ የኢንደስትሪዎች መስፋፋት እና ከእሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የግሪን ሀውስ ጋዝ ኢፌክት ለአለርጂ መከሰት እንደ ምክኒያትነት ይጠቀሳሉ።
ምልክቶች
የአለርጂ ምልክቶች እንደየመነሻ ምክኒያታቸው ይለያያኡ። ለምሳሌ አየር ወለድ ከሆኑ ነገሮች የሚነሳ አለርጂ ከሆነ ያለብን ሰውነታችን ምልክት የሚያሳየው ከተበከለ አየር ጋር ንኪኪ በሚፈተርበት ጊዜ ሲሆን ማሳል፣ ማስነጠነስ ፣ የአይን መቅላት እንዲሁም የትንፋሽ መቆራረጥ ሊያጋጥመን ይችላል።
ባንጻሩ ደግሞ ከምግቦች የሚመጣ አለርጂ የሆድ ህመም፣ ማስመለስ፣ የቆዳ ማሳከክ እንዲሁም የሰውነት ማበጥን ያስከትላል። እንዲሁም በተለያዩ እንስሳት መነደፍ ያ የተነደፍነውን አካባቢ እስከ 10 cm ርቀት ድረስ ከማበጥ ጀምሮ እንዲቀላ እና እንዲቆስል ያደርገዋል። ይህም ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት ውስጥ ሊቆይ ይችላል።
ህክምና
አለርጂን ለማከም እና የተፈለገውን ለውጥ በጊዜ የማግኘት እድላችን ህመሙን በትክክል መረዳት እና መንሴውን በማወቅ ይወሰናል። በርግጥ አለርጂን ከማከም ይልቅ እንዳይከሰት አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ የተሻለ አማራጭ ነው። አንዴ አለርጂው ከተከሰተ በኋላም የሚያስነሳብንን ነገር ለይቶ ማወቅ እና በተቻለ መጣን ያንን ነገር ከእኛ ማራቅ ይጠበቅብናል።
አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ለአለርጂ የሚያጋልጡ ምግቦችን በሳይንሳዊ መንገድ ጄኔቲክ እንጂነሪንግን (genetic engineering) በመጠቀም አለርጂ እንዲያመጡ ያደረጋቸውን ባህሪያቸውን ነጥሎ በማውጣት ምግቦቹን ነጻ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ ተስፋ ሰጪ የሆነ ውጤትም ታይቶበታል።
አለርጂ በብዙዎች ዘንድ እንደ ተራ የሚታይ ሲሆን ህይወት እስከመቅጠፍ ድረስ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ እና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ሀገራት ለነገሩ ሰፊ ትኩረት በመስጠት በአለርጂ ላይ ብቻ አተኩረው የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን አለርጂስት (Allergist) በመባል ይታወቃሉ። አለርጂስት ለመሆንም የ9 አመት ትምህርት እና ልምምድ ይጠይቃል። ለመጀመሪያ ጊዜ አለርጂ የሚለውን ስያሜ የሰጠው ሰውም ክሌሚንስ ቮን ፒርኬት የተባለ የባዮሎጂ እና የህጻናት ህክምና ባለሙያ ነው።
በዚህ ቪዲዮ ስለ አለርጂ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን። ከቪዲዮው ምን ተማራችሁ? እናንተ ወይም የምታውቁት ሰው ያለበት አለርጂ ምንድን ነው? በምን መልኩስ ነው ህክምና እያገኘ ያለው። ሀሳባችሁን አግሩን። ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን።