ዴጃቩ ወይም የቀን መመሳሰል እና ድግግሞሽ

አንዳንድ ጊዜ ከዚህ በፊት ሄዳችሁበት የማታውቁት ቦታ ላይ ልክ ከዚህ በፊት የምታውቁት ያህል ተሰምቷችሁ ያውቃል? ወይም ደግሞ አድርጋችሁ የማታውቁት ነገር ልክ አድርጋችሁት እንደምታውቁ ያህል ተሰምቷችሁ ያውቃል? በአለም ላይ ካለው ሰው ውስጥ ከ60-80% የሚሆኑት በህይወታቸው ቢያንስ ለአንድ ጊዜ እንዲህ ተሰምቷቸው ያውቃል። ይሄ ሁነት ዲዣ- ቩ በመባል ይታወቃል። 

ይሄ ሁነት ለመጀመሪያ ጊዜ ዲዣ- ቩ የሚለውን ስያሜ ያገኘው በፈረንሳዊው የፓራ ሳይኮሎጂ ተመራማሪ ኢምሊ ቦይራክ (Emlie Boirac) ነው። በፈረንሳይኛ ቋንቋ ዲዣ – ቩ ማለት “ከዚህ በፊት የታየ” እንደማለት ነው። ዲዣ – ቩ የህመም ስሜት ወይም የጤና ችግር አይደለም። በርግጥ በሳይንሳዊ ጥናት ትክክለኛ ምክኒያቱን ለማወቅ እስካሁን ድረስ አልተቻለም። ለዚህም ደግሞ ምክኒያቱ ታቅዶበት የሚመጥ ወይም በየወቅቱ የሚከሰት ነገር አለመሆኑ ነው። ሁኔታው የሚከሰትበት ጊዜ እና መገድ ቢታወቅ ነገሮችን በማመቻቸት ልክ ሲከሰት ክትትል እና ምርመራ በማድረግ ስለ ጉዳዩ ጠለቅ ያለ እውቀት ለማግኘት ይቻል ነበር።

ከዚህም የተነሳ ስለ ዲዣ – ቩ ያለን እውቀት ራሳቸው ሰዎቹ ስላጋጠማቸው ሁኔታ ከሚናገሩት በመነሳት ብቻ ነው። በርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የህክምና እና የስነ ልቦና ባለሙያዎች የተለያዩ መላ ምቶችን ለመስጠት ሞክረዋል። ሁሉም የሰጡት መላ ምት በተወሰነ መልኩ እውነትነት ያለው ቢመስልም ሙሉ በሙሉ ወደ ድምዳሜ ለመድረስ ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም። ከዚህ ባለፈም ምሁራኑ የሚሰጡት መላምት የማይገናኝ እና የተለያየ መሆኑ ስለነገሩ በሙሉ ልብ ለመናገር ከባድ ያደርገዋል።

ባለሙያዎች ከሚሰጧቸው ወደ 40 የሚደርሱ መላ ምቶች መካከል በሰፊው ተቀባይነት ያላቸው ሶስቱ ናቸው። የመጀመሪያው dual processing ነው። ይህም አዕምሯችን በተመሳሳይ ሰዓት ብዙ ነገሮችን እያስተናገደ ከሆነ እና አንዱ ጉዳይ ከሌላው ዘግይቶ ወደ አዕምሯችን ሲደርስ ሁኔታው ከዚህ በፊት አጋጥሞን የሚያው ያህል ይሰማናል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ሄዳችሁ ወደ ማታውቁት ሀገር ሄዳችሁ ወደ አንድ አዲስ ሬስቶራንት ስትገቡ  የሬስቶራንቱ የግድግዳ ቀለም፣ የወንበሮች ቅርጽ፣ የአስተናጋጆች ልብስ፣ የመሬቱ ወለል፣ የመብራቶቹ አይነት፣ የጠረጴዛው ልብስ እና ሌሎችም ጉዳዮች አይናችሁ ይመለከታል። እነዚህ እይታዎችም ወደ አዕምሯችሁ ዘልቀው ይገባሉ። ከእነዚህ መካከል ግን አንዱ እይታ ዘግየት ብሎ ወደ አዕምሯችሁ ከደረሰ እና ቆየት ብላችሁ ካስተዋላችሁት ነገር ግን ልብ ባትሉትም ቀደም ብላችሁ እንደገባችሁ ያያችሁት ከሆነ ምንም እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም ወደዚያ ሀገር ያቀናችሁት ከዚህ በፊት ያን ሬስቶራንት የምታውቁት ያህል ይሰማችኋል። ይህ የሆነው ቀድሞ አይናችን ያያቸው ግን ልብ ያላልናቸውን ነገሮች ከሰከንዶች ቆይታ በኋላ ስናስተውላቸው ነው።

ሁለተኛው መላ ምት ደግሞ ከህልም ጋር ቁርኝት አለው ተብሎ ይታሰባል።  ይኸውም በህልማችን ያየነው ነገር በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የሚመስል ሁኔታ ሲገጠመን የእውነት በአካል ከዚህ በፊት አጋጥሞን የሚያውቅ ይመስለናል። ብራውን በተባለ ሰው በ2004 የተደረገ ጥናት ህልሞች እና ዲዣ – ቩ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው አሳይቷል። 

ሶስተኛ መላ ምት ደግሞ ዲዣ – ቩ የሚከሰተው በተከፋፈለ ትኩረት ምክኒያት ነው ይላል። ለአንድ ነገር በቂ የሆነ ትኩረት ካልሰጠን አዕምሯችን ስለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ግልጽ አይሆንም። ይህም ነገሮችን የሚያስታውሰው የአዕምሯችን ክፍል በዚህ ሁኔታ ከዚህ በፊት አልፎ የሚያውቅ ይሁን አይሁን ለማስታወስ ይቸገራል።

ሳይንሳዊ የሆኑትን መላምቶች አነሳን እንጂ ምንም ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው እና ከሁኔታው ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በሳይንሳዊ መንገድ ምንም ፍንጭ የሌላቸው ብዙ ግምቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ reincarnation ወይም ዳግመ መፈጠር የሚባለው እሳቤ ነው። ልክ እንደ ህንድ ባሉ ምስራቃዊያን ሀገራት ዘንድ ዳግም መፈጠርን ብዙ ሰው ያምናል። ከዚህ በፊት በህይወት የነበረ ሰው ሲሞት እንደገና ተመልሶ እንደሚፈጠር እና  እንደሚኖር ያስባሉ። ከዚህ የተነሳም አንድ ሰው ዲዣ – ቩ የሚገጥመው ሰው ሁኔታውን ከዚህ በፊት በነበረው ህይወቱ ኑሮት ስለሚያውቅ ወይም አጋጥሞት ስለሚያውቅ ነው ይላሉ። ዳግም መፈጠር እንደ ሂንዱይዚም እና ቡድሂዝም ባሉ እምነቶች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ነገር ቢሆንም ምንም አይነት ሳይንሳዊ የሆነ ማስረጃ የለውም።

ከዚህ በተጨማሪም የትይዩ ህዋ ወይንም parallel universe ሀሳብ አራማጆች አሉ። እንደ parallel universe እሳቤ የእኛን አለም የሚመስል አለም ልክ አንተን እና አንቺን የሆኑ ሰዎች ያሉበት አለም አለ ተብሎ ይታሰባል። ዲዣ – ቩ በዚያኛው እኛን በሚመስለው አለም ያሉ የእኛ ኮፒዎች ያደረጉትን ነገር የምናይበት መስኮት ወይም ክስተት ነው ብለው ያስባሉ። በርግጥ የparallel universe መኖር ከተራ አፈታሪክ ያለፈ ሳይንሳዊ ትንታንኔ ያለው ነገር ቢሆንም ግን እስካሁን ድረስ በተጨባጭ ለመናገር የሚቻል ነገር የለም። 

የዲዣ – ቩን ምንምነት ለማጥናት በተደረገ ጥናት ውስጥ የተወሰኑ ሰዎች በስክሪን ላይ ከእንቅልፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቃላት እንዲያዩ ተደረገ። ከቃላቶቹ መካከል ትራስ፣ አልጋ፣ ፒጃማ፣ አንሶላ ፣ ብርድልብስ፣ ህልም፣ መንቃት ወ.ዘ.ተ አይነት ቃላትን አሁ ነገር ግን እንቅልፍ የሚለው ቃል ስክሪኑ ላይ አልነበረም። ሰዎቹ ስክሪኑን በተደጋጋሚ ካዩ በኋላ በስክሪኑ ላይ ያያችኋቸውን ቃላት ጻፉ ሲባሉ ወደ 70 % የሚሆኑቱ እንቅልፍ የሚለውን ቃል ጽፈው ነበር። ይሄ ቃል ምንም እንኳን ስክሪኑ ላይ ባያዩትም አዕምሯቸው ግን ከእንቅልፍ ጋር ተያያዥነት ያለውን ቃል በደጋጋሚ ስላየ በራሱ የእንቅልፍን እሳቤ በትውስታቸው ውስጥ ስሏል። ስለዚህ እንቅልፍ የሚለውን ቃል ያዩት ይመስላቸዋል።

ዣማ – ቩ (Jamais – vu) ሲባልስ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ዣማ – ቩ ማለት “ታይቶ የማይታወቅ” (Never Seen) ማለት ነው። ይህም የዲዣ – ቩ ተቃራኒ ሲሆን ከዚህ በፊት አጋጥሞን የሚያውቅ ነገር ስንረሳ ነው። ከዚህ በፊት አይተነው የምናውቀን ፊልም ስናየው ረስተነው ልክ እንዳዲስ አዕምሯችን ሲመዝዘግብ ዣማ – ቩ ተከሰተ ይባላል። የሚጥል በሽታ (Epilepsy) ያለባቸው ህሙማን በዣማ – ቩ የመጠቃት እድላቸው በጣም ሰፊ ነው።

ዣማ – ቩን ከዲዣ – ቩ በተሻለ በቀላሉ ለመመራመር እና ለማትናት ይቻላል። ይህም የሆነው የዣማ – ቩን ስሜት በቀላሉ መፍጠር ስለሚቻል ነው። ለምሳሌ እስቲ ከዚህ በፊትየምታውቁትን ቃል ደጋግማችሁ ጥሩ። ከብዙ ድግግሞሽ በኋላ ቃሉ ትርጉም ያጣባችኋል። ይህም የሚሆነው አዕምሯችሁ የነገሩን ትርጉም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ስለሚረሳ ነው። ምንም እንኳን ቃሉን እና ትርጉሙን ከዚህ በፊት ቢያውቀውም ለአፍታ ያህል ግን ይረሳዋል። በዚህም ምክኒያት ዣማ –  ቩ  ተፈጠረ ማለት ነው። 

ለምሳሌ፡ መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና መኪና … ለተወሰነ ሽራፍራፊ ሰከንድ እንኳን  መኪና የሚለው ቃል ትርጉም አላጣባችሁም?

የዛሬውን ቪዲዮ በዚህ አበቃን። ዲዣ – ቩ አጋጥሟችሁ ያውቃል? ገጠመኛችሁን አካፍሉን። ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን። 

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *