ርካሽ ነገር ውድ ነው ፤ ውድ ነገር ደግሞ ርካሽ ነው

ርዕሱን እንዲሁ በጨረፍታ ላየው ሰው ስህተት ሊመስል ይችላል። ምን ያህሎቻችሁ ግን የዚህን ነገር እውነታ ተገንዝባችኋል?

በዚህ ሁሉም ነገር ከዕለት ወደ ዕለት እየተወደደ እየጨመረ ባለበት ጊዜ ግዚዎቻችሁን እንዴት ነው የምትፈጽሙት? አብዛኛውን ጊዜ የምትገዙት ርካሽ የሆነ ዋጋ ያለውን ነገር ወይስ ውድ የሆነውን ነው የምትገዙት?

እንበል እና ጫማ ለመግዛት ፈልጋችሁ ወደ አንድ የጫማ መደብር አመራችሁ። በዚያም ሻጩ የተለያዩ የጫማ አይነቶችን አሳያችሁ። ባለ 400 ፣ 700፣ 1000፣ 1500 እና 2000 ብር ድረስ የሚያወጡ ነገር ግን አንድ አይነት ብራንድ ያላቸውን ጫማዎች አሳያችሁ። የትኛውን ትገዛላችሁ? ከፍተኛ ሂሳብ ያለውን ወይስ ዝቅተኛ ሂሳብ ያለውን?

ባለ 400 ብሩ ገንዘቡ አነስ ስለሚል ብቻ ከገዛችሁት ወር ሳይሞላው ከጥቅም ውጪ ይሆንና ሌላ ለመግዛት እንደገና ትሄድላችሁ። በድጋሜ ይህንኑ ስትገዙ እና ይህንኑ ሂደት ስትደጋግሙ አንዴ ደህና ነገር ላይ ማውጣት የምትችሉትን ወጪ በተደጋጋሚ ትንንሽ በሚመስሉ የገንዘብ መጠኖች ታወጣላችሁ።

ከዚህ እንደምንረዳው የአንድ ነገር ወይም ምርት ዋጋ ለሽያጭ በቀረበበት ወቅት የተጠየቀው የክፍያ መጠን ብቻ አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ዋጋ ማለት እቃውን ከገዛችሁት በኋላ የሚሰጣችሁ አገልግሎት ነው። በዚህ ላይ ሌላ ምሳሌ መውሰድ እችላለን። መኪና ለመግዛት ወጥታችሁ አነስተኛ ዋጋ ስላለው ብቻ ያረጀ ወይም ለብዙ ጊዜ ያገለገለ መኪና ብትሸምቱ በአመት ውስጥ ለመኪናው ከከፈላችሁት ሂሳብ በላይ እሱን ለመጠገን ታወጣላችሁ። ምናልባትም የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችል መኪናን አንዴ ጨከን ብላችሁ ገንዘባችሁን አውጥታችሁ ብትገዙ ግን ያለምንም ጭንቀት የተሻለ ርዝማኔ ላለው ጊዜ ያገለግላችኋል። ታዲያ ርካሽ ያላችሁት ነገር ውድ ሆነ ብዙ ወጪ አስወጣችሁ ፤ ውድ ነው ያላችሁት ነገር ደግሞ ደጋግማችሁ ከማውጣት ገላገላችሁ ማለት ነው። ለዚህም ነው ርካሽ ነገር ውድ ነው ፤ ውድ ነገር ደግሞ ርካሽ ነው የምንለው። ወይም ምዕራባዊያኑ እንደሚሉት “Cheap is expensive and expensive is cheap. “ 

ይሄ ብሂል ትንሽ ከሚባለው እስኪብሪቶ ግብይት ጀምሮ እስከ ቤት እና ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ድረስ ይሰራል። በግል እና በቤተሰብ ደረጃም በተለይም ከአመጋገብ ስርዓት ጋር በተያያዘ ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ነገር ግን ርካሽ የሆኑ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ያላቸውን ምግቦች የምናዘወትር ከሆነ ለዛሬው እያሰብን ያለነው ያተረፍነውን ሽርፍራፊ ሳንቲም ቢሆንም ወደ ሰውነታችን እየገባ የተጠራቀመው የኮሌስትሮል መጠን ግን በጊዜ ሂደን ለጤና እክል ይዳርገናል። ጤናችንን ለማስተካከልም ብዙ የህክምና እና የመድሀኒት ወጪዎችን ማውጣት ይጠበቅብናል። አልፎ ተርፎም በዚህ ምክኒያት የደረሰብን በሽታ ህይወታችንን እስከመንጠቅ ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን በጊዜ አመጋገባችንን ብናስተካክል እና ዛሬ ላይ ርካሽ ከሆኑ ነገሮች ይልቅ ለጤና ተስምሚ ነገሮችን የሆነ ያህል ገንዘብ ጨምሮ መመገብ ብልህነት ነው።

በህክምናም ቢሆን በቀላሉ መታከም የሚችልን ነገር በጊዜው ገንዘብ ላለማውጣት ሲባል ብቻ ተገቢውን የህክምና ክትትል ባያገኝ ነገ ላይ ነገሩ ሲከፋ እና ህክምና ማግኘቱ የሞት እና የህይወት ጉዳይ ሲሆን ለብዙ ወጪ መዳረጉ አይቀርም።

ነገር ግን አንድ ነገር ደግሞ ውድ ነው ማለት ለረዥም ጊዜ ማገልገል የሚችል እና ጥሩ እቃ ነው ማለት አይደለም። እጅግ ብዙ መዋለ ንዋይ ፈሰስ ተደርጎባቸው አገልግሎታቸው ግን እምብዛም የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ምክኒያቱም አንዳንድ ጊዜ እቃው ከሚያወጣው በላይ እንዲሁ የመሸጫ የገንዘብ ተመን የሚያወጡ ሰዎች አሉ። ከዚህ በተጨማሪም እንዲሁ ውድ ነገሮችን መግዛት እና መሰብሰብ የሚወዱ ሰዎች አሉ። ውድ ነገር አገልግሎቱን ሳይሆን ውድነቱን ብቻ አይተን የምንገዛ ከሆነም ትርጉም አልባ ወጪ ነው የሚሆነው።

ምክኒያቱም የአንድ ነገር መወደድ ወይም መርከስ የእቃውን ትክክለኛ ዋጋ ላይተምን ይችላል። አንዱ ራሱ እቃ ከሱቅ ሱቅ የተለያየ የገንዘብ መጠን ሊተመን ይችላል። በተለይም እንደኛ ሀገር ባሉ አብዛኛው ምርቶቻቸው ቋሚ የሆነ የመሸጫ ዋጋ ወይም fixed price በስፋት በማይዘወተርባቸው አካባቢዎች የምርቶች የዋጋ መጠን ከሱቅ ሱቅ እንዱሁም ከከተማ ከተማ ሊለያይ ይችላል። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም እቃው አንድ አይነት እስከሆነ ድረስ አነስ ያለ ገንዘብ የሚጠይቀውን መግዛት ችግር የለውም።

በአንጻሩ ደግሞ ርካሽ የሚባሉ ወይም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ሁሉ ምንጊዜም ጥሩ አይደሉም ብለን ለመደምደም አንችልም። ክፍያቸው መጠነኛ የሆነ እና ለረዥም ጊዜ ሊያገለግሉ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ የማይካድ ሀቅ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ግን ቀላል የሚመስል ወጭዒ መጀመሪያ ላይ የሚጠይቁ እና በኋላ ላይ እጅግ ብዙ ተጨማሪ ዋጋ የሚያስከፍሉ ነገሮች ደግሞ አሉ።

አንድን ነገር ስንገበይ ርካሽ ስለሆነ ብቻ ከሚለው እሳቤ ተነስቶ መግዛት አለማስተዋል ነው። ውድ ስለሆነ ብቻ ጥሩ ነው ብሎ መግዛት ደግሞ ሞኝነት ነው። ከዚህ እንደምንረዳው ዋናው ነገር የአንድ ምርት ወይም እቃ ዋጋ የተለጠፈበትን ወይም የተጠየቀውን ያህል ብቻ እንዳልሆነ ነው። ስለዚህ ምንጊዜም ቢሆን ማንኛውንም ነገር ከመግዛታችን በፊት ጊዜ ወስዶ ማሰብ ተገቢ ነው። 

በርግጥ አንዳንዴ በጣም ስንፈልግ የነበረውን ነገር በቅናሽ ዋጋ አለ እዚህ ይገኛል ሲባል አይቶ ማለፍ ሊከብድ ይችላል። አንዳንድ ጊዜም “ታላቅ ቅናሽ እዚህ ይገኛል” የተባለባቸው ቦታዎች ላይ አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው ከመሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ የተደረገ ሊመስላቸው ይችላል። ነገር ግን በንግዱ አለም ያሉ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት ከመሸጫ ዋጋው ላይ ሳይሆን ከትርፉ ላይ የተወሰነ በመቀነስ ነው።

የንግድ እና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስተምሩት የአንድ ነገር ትክክለኛ ዋጋ የሚመዘነው በሚጠየቀው የሽያጭ ዋጋ ሲካፈል ለሚሰጠው የአገልግሎት ጊዜ ነው። ከዚህም በመነሳት በምታደርጉት ግብይቶች ሁልሉ ትንሽም ሆኑ ትልልቅ የነገሩን የሽያጭ ዋጋ፣ የእቃውን ጽናት እና ጥንካሬ እንዲሁም ከግብይት በኋላ ሌሎች ተከታይ ወጪዎችን ያስወጣል ወይስ አያስወጣም የሚለውን ሁሉ ማጤን ያስፈልጋል። 

ቅናሽ ሁሉ ቅናሽ አይደለም ምናልባትም ከኋላው ተጨማሪ ወጪዎችን ይዞ ይመጣል እና የብልህነት ውሳኔ መወሰን ተገቢ ነው።

በዚህ ጨረስን። ከዚህ ቪዲዮ ምን ያህል ትምህርት አገኛችሁ? ከዚሁ ጋር የተያያዘ ገጠመኝ ካላችሁ አካፍሉን።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *