የስኳር ህመም መሰረታዊ ትምህርቶች
ትርጓሜ፦ የስኳር ህመም ማለት በደማችን ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን መጨመር ማለት ነው።
የህመሙ ስርጭት፦ በአለማችን ብሎም በሀገራችን በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በአማካኝ ከ አስር ሰወች አንድ ሰው የስኳር ህመም አለበት ተብሎ ይገመታል።3/4 የሚሆነው ታማሚ በታዳጊ ሀገሮች ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ህመሙ እንዳለባቸው አያቁም።
የስኳር ህመም አይነቶች
1) አይነት አንድ የስኳር ህመም
2) አይነት ሁለት የስኳር ህመም
3) በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር ህመም
4) ሌሎች የስኳር ህመሞች
የህመሙ ምልክቶች፦ ምንም አይነት ምልክት ሳይኖረው በደም ምርመራ ብቻ ሊታወቅ ይችላል። ቶሎ ቶሎ ውሀ የመጥማት ፣ቶሎ ቶሎ የመሽናት ፣ የረሀብ ስሜት ፣ ክብደት መቀነስ ፣የድካም ስሜት እና በሌሎች ኢንፌክሽን የመጋለጥ ምልክቶች ይኖራቸዋል ። በጣም ከፍተኛ የስኳር መጠን ደግሞ ራስን እስከመሳት ሊያደርስ ይችላል። እንዲሁም ስኳር በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ማለትም የልብ፣ የኩላሊት፣ ስትሮክ ፣ የአይን ፣ የእግር ቁስለት ጉዳት ካደረሰ በኋላ ሊታወቅ ይችላል።
ቅድመ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ሰወች
1) ማንኛውም ከ40 አመት እድሜ በላይ ያለው
2) ከልክ በላይ ውፍረት
3) የደም ግፊት ህመም ያለባቸው
4) በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ የስብ መጠን መኖር
5) በህክምና የታወቀ የጭንቅላት ወይም የልብ የደም ስር መጥበብ
6) የ ኤች አይ ቪ ህመም ያለባቸው
7) ከ 4 ኪ.ግ ክብደት በላይ የሚመዝን ህፃን የወለደች እናት
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች ያለባቸው ሰወች በየሶስት አመት የስኳር መጠን እንዲመረመሩ ይመከራል። ነገር ግን መጠነኛ መጨመር ካሳየ በየአመቱ እንዲለካ ይደረጋል።
የስኳር ህመም ምርመራ ማረጋገጫ
1) ከምግብ በፊት(ለ 8 ሰዓት ምግብ ሳይወሰድ)- 126 እና ከዚያ በላይ
2)የ3 ወር የስኳር አማካይ ምርመራ(HGA1c) -6.5 እና ከዚያ በላይ
3)75 ግራም ስኳር ከወሰዱ 2 ሰዓት በኋላ ያለው ልኬት- 200 እና ከዚያ በላይ
ወይም
4) የስኳር ምልክት የታየባቸው ከሆነ በማንኛውም ሰዓት የሚለካ የስኳር መጠን- 200 እና ከዚያ በላይ ከሆነ የስኳር ህመም አለ ይባላል።
የስኳር ምርመራ ለሁለተኛ ጊዜ በድጋሜ ከሌላ ወይም ከተመሳሳይ የደም ናሙና መለካት እና መረጋገጥ ይኖርበታል።
የስኳር ህመም ህክምናወች
1) አጠቃላይ ጤና አጠበባባቅ በሳምንት 150 ደቂቃ መካከለኛ እንቅስቃሴ (የፍጥነት ጉዞ፣ እርሻ…) ማድረግ (ሁለት ተከታታይ ቀናት ሳይሰሩ ማሳለፍ አይመከርም)
ከእንቅስቃሴ በፊት የስኳር መጠን መለካት ሊያስፈልግ ይችላል
ከ 30 ደቂቃ በላይ ምንም ሳይንቀሳቀሱ ቁጭ አለማለት (የተወሰነ እንቅስቃሴ በመካከል ያስፈሊጋል)
ኮምፕሌክስ ካርቦሀይድሬት ያላቸው(ድንች ፣ፖስታ፣ ዳቦ፣ መኮረኒ…)መካከለኛ ማድረግ
የአትክልት ምግቦችን ማዘውተር
ስኳር ቶሎ ሚጨምሩ(ስኳር፣ለስላሳ፣ማር፣ ኬክ ..)አለመመገብ
ጎጅ ስብ ያለባቸው (ቅቤ፣የረጋ ዘይት..) መቀነስ
ጨው ፣አልኮል መቀነስ እና ሲጋራ/ትምባሆ አለማጨስ
ከፍተኛ ውፍረትን ቢያንስ በ 5 % መቀነስ
፨በቂ እንቅልፍ መተኛት
፨ ኮቪድ 19 እና ሌሎች ክትባት መውሰድ
2) መድሀኒት በመውሰድ
፨ የሚዋጥ መድሀኒት- ለአይነት ሁለት ስኳር ህመም የሚሰጡ መድሀኒቶች ናቸው።
፨ መርፌ(ኢንሱሊን)- ይህ ደግሞ ለአይነት አንድ ስኳር ፣ በእርግዝና ጊዜ እና በመድሀኒት መቆጣጠር ያልተቻለ ወይም የስኳር መጠኑ በጣም የጨመረ አይነት ሁለት የሰኳር ህመም እንዲወስዱ ይደረጋል። ኢንሱሊን በፍሪጅ ወይም አሸዋ ውስጥ ውሀ በመጨመር ማስቀመጥ ይኖርብናል። ኢንሱሊን የሚወጋበትን የሰውነት ክፍል( ትክሻ፣ሆድ ፣ጭን ) በየጊዜው መቀያየር አለብን።
ህክምና ላይ እያሉ የሚፈለገው የስኳር መጠን
1) ምግብ ሳይበሉ (ላለፉት 8 ሰዓታት) የሚለካ መጠን ከ 80-130 ሚ.ግ/ዴ.ሊ
2) ምግብ ከተበላ 2 ሰዓት በኋላ የሚለካው መጠን ከ 180 ሚ.ግ/ዴ.ሊ በታች እና
3) የሶስት ወር አማካኝ ምርመራ ልኬት ለአብዛኛው ማህበረሰብ ከ 7% በታች መሆን ይኖርበታል።
በእርግዝና ጊዜ የሚደረግ የስኳር መጠን ክትትል
1) ምግብ ከመመገብ በፊት( ለ8 ስዓት) የሚለካው መጠን ከ 95 ሚ.ግ/ዴ.ሊ በታች
2) ከምግብ 1 ሰአት በኋላ የሚለካው መጠን ከ 140 ሚ.ግ/ዴ.ሊ በታች
3) እና ከምግብ 2 ሰአት በኋላ የሚለካው መጠን ከ 120 ሚ.ግ/ዴ.ሊ በታች መሆን ይኖርበታል ።
ማስታወሻ ፦ ከእርግዝና በፊት የሶስት ወር አማካይ የስኳር መጠን ልኬት ከ6.5 % በታች መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ ሀኪምዎን ከእርግዝና በፊት ማማከር ይኖርብዎታል።
የስኳር መጠን ክትትል
፨ እንደ ስኳር መጠኑ በየወሩ ወይም በየ ሶስት ወር ክትትል ያስፈልጋል።
፨ በቤት ውስጥ መለካት የሚችሉ ከሆነ
፨ ኢንሱሊን ለሚወስዱ- ምግብ ሳይበሉ ጥዋት ፣ከምግብ በፊት፣ የስኳር መጠን መቀነስ ምልክት ሲኖር እና ከምግብ 2 ሰዓት በኋላ በተቻለ መጠን መለካት
፨ የሚዋጥ መድሀኒት ለሚወስዱ – የምግብ፣ የእንቅስቃሴ ወይም የመድሀኒት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ መለካት ያስፈልጋል።
፨ የሶስት ወር አማካይ ምርመራ ደግሞ በአመት ከ 2-4 ጊዜ መለካት ይመከራል።
ሌሎች በየክትትል ጊዜ መከናወን ያለባቸው ነገሮች
፨ የግፊት ምርመራ
፨ የእርግዝና ሁኔታ
፨የልብ ህመም ቅድመ መከላከል
፨ የደም ውስጥ የስብ ክምችት መጠን (እንደ አስፈላጊነቱ)
፨ የውፍረት መጠን(ክብደትና ቦርጭ)
፨ የቫይታሚን ቢ 12 መጠን (እንደ አስፈላጊነቱ)
በየአመቱ መደረግ ያለባቸው ክትትል
እነዚህ ክትትሎች የሚያስፈልጋቸው ለአይነት ሁለት ታካሚወች ስኳር ህመም ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ለ አይነት አንድ ደግሞ ስኳር ህመም ከታወቀበት 5 አመት በኋላ ይጀመራል።
፨ የእግር ቁስለት(በሀኪም የመረመር)
፨ የአይን ምርመራ(የመጀመሪያው ምርመራ ጤነኛ ከሆነ በየ 2 ወይም 3 አመት ማድረግ ይቻላል)
፨ የሽንትና ኩላሊት ምርመራ
፨ የልብ ህመም ክትትል
የእግር ቁስለት ለመከላከል መደረግ ያለባቸው
፨ በየቀኑ መከታተል
፨ ለብ ባለ እንጅ በሞቀ ውሀ አለመታጠብ
፨ እንዳይሰነጣጠቅ ቅባት መቀባት
፨ ጥፍርን በጥንቃቄ መቁረጥ
፨ ካልስ በየጊዜው ወቀየር
፨ ጫማ ከመልበስ በፊት ጠጠር ወይም ሌላ ጎጅ ነገር አመኖሩን ውስጡን በደንብ ማየት
፨ በባዶ እግር አለመንቀሳቀስ
፨ የስኳር መጠንን መቆጣጠር እና አለማጨስ ይኖርብናል።
የስኳር መጠን መቀነስ
ይህ ህመም አደገኛ ሲሆን የስኳር መጠን ከ70 ሚ.ግ/ዴ.ሊ በታች ሲሆን ይከሰታል። ምክንያቶቹ ደግሞ በቂ ምግብ ባለመውሰድ፣የመድኃኒት መጠን መብዛት ፣ከባድ እንቅስቃሴ በመስራት እና ተያያዥ የኩላሊት ወይም የጉበት ህመም ሲኖር ሊከሰት ይችላል።
የስኳር መቀነስ ምልክቶች ራስ ምታት፣ ረሀብ፣ ጭንቀት፣ ልብ በፍጥነት መምታት፣ ላብ፣ የሰውነት መንቀጥቀጥ እና ራስ መሳት ናቸው። እነዚህ ምልክቶች ከተሰሙ ወዲያውኑ 4 የሻይ ማንኪያ ስኳር ወይም 4 ከረሚላ ወይም ግማሽ ብርጭቆ ለስላሳ መውሰድ ያስፈልጋል። ከ 15 ደቂቃ በኋላ ምልክቶች ከቀጠሉ ድጋሜ መውሰድ እና ሆስፒታል መሄድ ያስፈልጋል።
ዶ/ር ክብረት እንየው ፤ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት