ገንዘብ ጥሩ አገልጋይ መጥፎ ጌታ ነው ይባላል። ጥሩ አገልጋይ ያስባለው በአግባቡ ጥቅም ላይ ካዋልነው የፈለግነውን የምንሸምትበት፣ ህልማችንን የምናሳካበት፣ መሰረታዊ ፍላጎቶቻችንን የምናሟላበት፣ ለጤናችን የሚያስፈልጉ መድሀኒቶችን የምንገዛበት ከዚህም አልፎ የምንዝናናበት፣ የምናጌጥበት መልሰን ስራ ላይ ብናውለው ደግሞ የምናተርፍበት መሆኑ ነው። መጥፎ ጌታ ያስባለው ደግሞ ከመገልገያነት አልፎ እኛነታችንንን የሚገዛ ከሆነ አዕምሯችን ከሰባዊነት ይልቅ ገንዘብን በልባችን ካነገሰ ጨካኞች፣ ለሰው ደንታ ቢሶች፣ ምግባረ ብልሹ እና አባካኞች ማድረስጉ ነው። አብረው የበሉ የጠጡ አብረው ያደጉ ሰዎች በገንዘብ ሲካሰሱ ጦር ሲማዘዙ ፣ ሀገራት ገንዘብን ብለው የረዥም ጊዜ ወዳጃቸው የነበሩ ሀገራትን ሲወሩ ማየት የአለማችን የተለመደ ገጽታ ሆኗል። ታዲያ ገንዘብ ጌታችን እንዳይሆን ይልቁንም ጥሩ አገልጋያችን እንዲሆን አያያዙን ማወቅ እና እሱን የማስተዳደር ችሎታን ማካበት ይገባናል።ገንዘብን ለጥቅማችን ማዋል ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ቁጠባ ነው። በርግጥ አብዛኛው ሰው የቁጠባን ምንነት እና አስፈላጊነት እጅግ ብዙ ጊዜ በተለያዩ አማራጮች ሰምቶታል። የብዙ ሰው ችግር ስለ ቁጠባ አስፈላጊነት አለማወቅ ሳይሆን ይሄንን ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ነው ።
ገንዘብን መቆጠብ በተለይም ደግሞ በፍጥነት ማስቀመጥ መቻል ሁሉንም ሰው የሚጠቅም ነገር ነው። ገንዘባችንን እንድንቆጥብ የሚያነሳሱን ብዙ መልካም ምክኒያቶች አሉ። ምናልባትም ድንገተኛ ወጪ አጋጥሟችሁ ይሆናል ወይንም ደግሞ ጓደኞቻችሁ የጉዞ ግብዣ አቅርበውላችሁ ይሆናል ወይም ቤት ለመግዛት ፈልጋችሁ ይሆናል ካልሆነም ደግሞ እንዲሁ ለአደጋ ጊዜ ብላችሁ አስቀድማችሁ ለመዘጋጀትና ካልተጠበቀ ወጪ ለመዳን ፈልጋችሁ ይሆናል። ምክኒያታችሁ ምንም ቢሆን ገንዘብ ልትቆጥቡ የምትችሉባቸው ብዙ አይነት መንገዶች አሉ። ሲታዩ እጅግ ቀላል የሚመስሉ እና የቁጠባ ባህላችሁን ለማዳበር የሚጠቅሟችሁ ነገሮችን እነሆ ለናል እስከመጨረሻው ድረስ ተከታተሉን።
ገንዘብ እንዳገኛችሁ ወዲያው ለምን ለምን እንዳዋላችሁት እንኳን ሳታውቁ በቀናት እንድሜ ውስጥ የት እንደገባ ነኳን ሳታውቁት አልቆባችሁ ያውቃል? የአብዛኛው ሰው መልስ አዎ ነው። ለዚህም ምክኒያቱ ደግሞ ወጪውን የሚመዘግብ ሰው ቁጥር እጅግ አናሳ መሆኑ ነው። የመጀምሪያው ገንዘብን ለመቆጠብ የሚረዳ መንገድ ወጪን መመዝገብ ነው። ወጪያችሁን መመዝገብ ከምን ላይ መቆጥብ እንደምትችሉ ፍንጭ ይሰጣል። ለአንድ ወር ያህል የምታወጡትን ሁሉ ብትመዘግቡ ገንዘባችሁን ምን ምን ላይ እያጠፋችሁ እንደሆነ እንድታውቁ ይረዳችኋል። ገንዘባችሁን ምን ላይ እያዋላችሁ እንደሆነ ካወቃችሁ እና የትኛውን ወጪያችሁን መቀነስ እንደምትችሉ ከተረዳችሁ በኋላ የበጀት እቅድ ማውጣት በበጀታችሁ መሰረት መንቀሳቀስ ትችላላችሁ። መጀመሪያ ላይ ሲታይ አድካሚ ቢመስልም ይህ ለመተግበር በጣም ቀላል የሆነ እና ለመቆጠብ ደግሞ አዋጪ የሆነ መንግድ ነው።
ሌላው ገንዘብን የመቆጠብ ልምድ እንድታካብቱ የሚረዳችሁ ነገር ብድራችሁን በጊዜ መክፈል ነው። ከግለሰብም ሆነ ከባንክ ብድር ካለባችሁ ገንዘባችሁን ከምታስቡት በላይ እያባከናችሁ ነው። ብድር የገንዘብ ነጻነታችሁን በመንፈግ በቀጣይ ገንዘብ ባገኛችሁ ጊዜ እንኳን ለራሳችሁ እንዳታውሉት ይልቁንም እሱን በመክፈል ሂደት እንድትታሰሩ ያደርጋል። ስለዚህ እጅግ አንገብጋቢ እና አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ለትንሹም ለትልቁም አትበደሩ። የዛሬ መበደር ለነገ የመክፈል ግዴታን ያመጣል። ነገ ላይ ደግሞ ብሩ ለሌላ ነገር አስፈልጓችሁ ሳለ ለቀድሞ ብድራችሁ የመክፈል ግዴታ ውስጥ ተገባላችሁ ስለዚህ ወር ከወር ብድር ከፋዮች እንጂ አትራፊዎች አትሆኑም። የቱንም ያህል አበዳሪያችሁ ፈታ ያለ ሰው እና ሰፊ ጊዜ ወስዳችሁ መክፈል እንደምትችሉ ተስፋ ቢሰጣችሁም ከምንም በፊት ብድራችሁን መክፈል ግን ተቀዳሚ ተግባራችሁ ሊሆን ይገባል። ሲቀጥልም ራሳችሁን ከፍተኛ የሆነ የወለድ ተመን ካላቸው ብድሮች ነጻ ማድረግ አለባችሁ።
በቤታችን በሚገኙ ነገሮች በቀላሉ ማዘጋጀት የምንችለውን ችፕስ ከውጪ በአስር ብር አንገዛለን ፣ ለአንዲት ስኒ ቡና 20 እና 30 ብር እናወጣለን በቤታችን በእጅጉን ከዚህ ባነሰ ወጪ ጀበና ሙሉ ቡና ማፍላት እንችላለን። አያችሁ አይደል በየቀኑ ለምቾት ሲባል ምን ያህል አላስፈላጊ ወጪዎች እንደሚወጡ? በመሆኑም በቀን ውስጥ የራሳችሁን ምግብ ለማብሰል እና ትኩስ ነገር ለማዘጋጀት ጊዜን መውሰድ፣ ቤትውስጥ የተበላሹ ነገሮችን በራሳችሁ መጠገን ፣ እቃችሁንና ልባሳችሁን ራሳችሁ ማጠብ ከአላስፈላጊ ወጪዎች እንድትቆጠቡ ይረዳችኋል። ከዚህ ባለፈ ብራድን ልብስ እና ጫማዎችን የማዘውተር አባዜ ካለባችሁ እሱን ብትቀንሱ መልካም ነው። መልበስ መዘነጥ ጥሩ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በቂ ነገር እያለን አንድን ነገር ብዙ ሰዎች ስላደረጉት ብቻ በዚህ ተነሳስተን በየጊዜው ገንዘባችንን የምናወጣ ከሆነ ገነዘብ አይበረክትልንም። ስለዚህ ለቅንጦት የምታወጡትን ወጪ መቀነስ ከተቻለም ደግሞ ማቆም የቁጠባ ባህልን ለማዳበር እጅግ ወሳኝ ነው።
ከብድር ባለፈ በአሁኑ ዘመን ባለው ቢዚ በሆነ ህይወትና በተደራረቡ ፕሮግራሞች አንዳንድ ክፍያዎችን በጊዜው ላንከፍል እንችላለን። አብዛኛው ድርጅቶች ደግሞ ዘግይተው በሚከፈሉ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ የቅጣት ክፍያን ይጨምራሉ። በርግጥ እንዲሁ ስናየው አሁን የተጣለብን የቅጣት ክፍያ እዚህ ግባ የማይባል ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን እንዲህ አይነት ወጪዎች ተደማምረው ኪሳችንን ማመናመናቸው አይቀርም። ስለዚህ ክፍያዎች በሙሉ በተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ እንዲከፈሉ ቢቻል በባንክ በኩል መከፈል የሚችሉትን ባንኩ በየወሩ እንዲከፍልልን ማድረግ አስፈላጊ ነው። ክፍያዎችን በጊዜያቸው መክፈል መቻል ደግሞ ገንዘባችንን በአግባቡ ለመጠቀም እና ለመቆጠብ የሚያስችል አይነተኛ መንገድ ነው።
እንደ CBE Birr፣ Tele Birr ያሉ ብዙ የክፍያ አማራጮች እና የATM ካርድ አገልግሎቶች መኖራቸው ለድንገተኛ ወጭዒዎቻችን ደራሽ ከመሆናቸውም በላይ ገነዘብን በጥሬው ይዞ ከመንቀሳቀስ እንደገላገሉን ግልጽ ነው። ነገር ግን እነዚህ አማራጭች ገነዘብን በቀላሉ እንድናወጣ እድል በማመቻቸታቸው ገንዘባችን የት እንደገባ ሳናውቀው ለትንሹም ለትልቁም ወጪ እናደርጋለን። ነገር ግን ገንዘብ አስፈላጊ በመሰለን ቁጥር ከማውጣት ይልቅ የተወሰነ ጥሬ ገንዘብ ይዞ መንቀሳቀስ ጥሩ ነው። ገንዘብን በጥሬ ይዛችሁ ከሆነ አንድ ነገር ልትገዙ ስትሉ አዕምሯችሁ ምን ያህል ገነዘብ ኪሳችሁ ወስጥ እንደቀረ በፍጥነት ስለሚረዳ ያገኛችሁትን ሁሉ ከመግዛት እና ገንዘባችሁን ከማባከን እንድትቆጠቡ ይረዳችኋል። ይህንን ለተወሰኑ ሳምንታት ተግባራዊ ብታደርጉ ምን ያህል ወጪያችሁ እንደሚቀንስ ማስተዋል ትችላላችሁ። እንዲሁ በካርድ ከምታወጡት ይልቅ ጥሬ ገንዘብን በእጃችሁ ይዛችሁ ማውጣታችሁ ደግሞ ስለምታወጡት እያንዳንዱ ወጪ በንቃትና በጥንቃቄ እንድታወጡ ያግዛችኋል።
ሌላው ገነዘብን በጥሬው ከመጠቀም በተጨማሪ ወደ ገበያ ከመሄዳችሁ በፊት ለመግዛት የሚያስፈልጓችሁን እቃዎች ዝርዝር አስቀድሞ ማውጣት ገንዛባችሁን እንድትቆጥቡ በጣም ይረዳችኋል። ዝርዝሩን ማውጣታችሁ የሚያስፈልጋሁን ነገሮችን ብቻ በመግዛት ያማራችሁን ሁሉ ከመግዛት እንድትቆጠቡ ያግዛችኋል። ወደ ገበያ ከሂዳችሁም በኋላ ያያችሁት ሁሉ አይመራችሁ፤ አስቀድማችሁ የዘረዛችኋቸውን ነገሮች ብቻ ገብይታችሁ ተመለሱ። በገበያ ውስጥም ብዙ አትቆዩ ዝርዝራችሁ ላይ የተቀመጡትን ነገሮች ብቻ በመግዛት ቶሎ ከገበያው ውጡ።ይህንን ስታደርጉ በገበያው ያላችሁ የቆይታ መጠን ትቀንሳላችሁ። ይህም ደግሞ የሚያምሩ ነገሮችን እያያችሁ ያማራችሁን ሁሉ ከመሸመት ይታደጋችኋል።
Tip በተጨማሪም ወደ ገበያ ከመሄዳችሁ በፊት ምግብ በደንብ ብሉ። ሆዳችሁ ሙሉ ሆነ ከሄዳችሁ የምታዩአቸው ነገሮች ያን ያህል አጓጊ አይሆኑባችሁም። ይሄ ማለት ገንዘባችሁ ከአላስፈላጊ ወጪ ተረፈ ማለት አይደል?
በጣም የምትወዱትና የምትከታተሉት የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከምታስቡት በላይ በምትገዙት ነገሮች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። ምክኒያቱም በገጹ ላይ ያያችሁት የታዋቂ ሰዎች ፎቶ፣ የለበሱት ልብስ፣ ያደረጉት ጫማ፣ የበሉት ምግብ እና የተዝናኑበት ቦታ የመሄድ እና እነሱ ያደረጉትን የማድረግ ፍላጎት ሳታስቡት በውስጣችሁ ያድራል። ያንን ለማድረግ ደግሞ አላስፈላጊ ገንዘብ ታወጣላችሁ። በማህበራዊ ሚዲያ የምትከታተሏቸው ሰዎችም ሆን ተብሎም ሆነ በአጋጣሚ ምክኒያት ምን መወሰንና ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ሊመክራችሁና ሊገፋፋችሁ ይችላሉ። ስለዚህ እናንተ ያያችሁትን ሁሉ ለመግዛት መነሳሳት የለባችሁም። ከዚህ በተጨማሪም አዲስ ምርት ገበያ ላይ በሚወጣ ጊዜ እንዳያመልጠኝ ከሚል ስሜት ራሳችሁን ልትጠብቁ ይገባል። እንዳያመልጠኝ የሚል ስሜት አዳዲስ ነገሮች ሁሉ ስያመልጥን እንድንገዛ ያነሳሳን እና ምናልባትም ያንን ነገር ከገዛነው በኋላ ያን ያህል የወጣበትን ገንዘብ ያህል ለኛ ጠቅም የሌለው ይሆናል። እስቲ ራሳችሁን ጠይቁ የምትገዟቸው ነገሮችን ሁሉ የምትገዙት አስፈላግጊ ስለሆኑ ነው ወይስ የሆነ ሰው ያደረገውን ነገሮች ሁሉ ለማድረግ ነው? የራሳችሁ የሆነ ግብ አዘጋጁ እና ለሱ ብቻ ተግታችሁ ስሩ። የሌሎች ሰዎችን ኑሮ ለነሱ ተዉላቸው። ስለዚህ ሰዎች ያደረጉትን ነገር እያዩ እኔስ ለምን ይቀርብኛል ከሚል ስሜት መቆጠብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አሮጌ ነገርን ለመተካት ሲያስፈልግ ብቻ አዲስ ነገርን መግዛትን መልመድ ጥሩ አማራጭ ነው። አንዳንድ እቃዎች ገበያ ላይ ስለተገኙ እና የሚሸጡ ስለሆኑ ብቻ የምትገዙ ከሆነ ይህንን ልማድ ልታቆሙ ይገባል። ምክኒያቱም ገንዘባችሁን በከንቱ እያወጣችሁ ስለሆነ። ምንም ነገር ከመግዛታችሁ በፊት ነገሩ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋችሁ፣ በብዛት ስንት እንደሚያስፈልጋችሁ እና ከዚህ በፊት ስንት እንዳላችሁ አስቡ። እናም አሁን አዲስ የመግዛትን አስፈላጊነት አስቡበት።
በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ግብይት በሚያደርጉ ጊዜ በመከራከር ያስቀንሳሉ። ይህ በወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነገር አይደለም። ይጠይቃሉ ፣ የተጠየቁት ያህል ገንዘብ በኪሳቸው ካለ ከፍለው ይሄዳሉ። በርግጥ አንዳንድ ነገሮች የተወሰነ ዋጋ ስላላቸው ለመደራደር ባንችልም ሌሎች ግብይቶችን ስናደርግ መደራደርና ዋጋ ለማስቀነስ መሞከር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በርግጥ መደራደሩ ጊዜያችንን ሊወስድብን ይችላል። በመደራደር ያሳለፍነው ጊዜ የከሰረ ጊዜ አይደለም። ምክኒያቱም ወጪያችንን በመቀነስ ገንዘባችንን እንድንቆጥብ በእጅጉ ስለሚረዳን። ከዚህ በተጨማሪ የፈለጋችሁን እቃ ሌሎች ሱቆች ጋር ያለውን የዋጋ ልዩነት ማነጻጸር ከምታስቡት በላይ ገንዘባችሁ እንዳይባክን እና እንድትቆጥቡ ይረዳችኋል። ስለዚህ አንድ ነገር እንደጠየቃችሁ ወዲያው ከመግዛት ይልቅ ረጋ ብላችሁ የእቃዎችን ዋጋ አነጻጽራችሁ እና ከተመሳሳይ ሱቆች ዋጋ ጋር አስተያይታችሁ መግዛቱ ገንዘባችሁን በከንቱ እንዳታወጣ ይጠቅማችኋል።
ራስን መገደብ እና ይህንን discipline ራስን ማሰልጠን ከቁጣባ ባለፈ በሁሉም የህይወታችሁ አቅጣጫ ከምታስቡት በላይ ጠቃሚ ነው። እስቲ ይህንን አማራጭ ሞክሩት እና ውጤቱን እናንተው መስክሩ። ነገሩ እንዲህ ነው ምንጊዜም ቢሆን አንድን ነገር የመግዛት ሀሳብ አዲስ ጫማ፣ አዲስ ስልክ ወይንም መኪና ሊሆን ይችላል ሲሰማችሁ ራሳችሁን ከልክሉ። እቃውንም አንስታችሁ በእጃችሁ ይዛችሁ ከሆነ አስቀምጡትና ከገበያው ዘወር በሉ። ወደ ቤት እንደገባችሁም አንዲት ወረቀት ውሰዱ እና የቅድሙን እቃ ስም፣ የትኛው የገበያ ቦታ/ሱቅ/ እንዳገኛችሁትና የእቃውን ዋጋ መዝግቡ። ቀኑንም አብራችሁ ጻፉ እና ይህንን ፅሁፍ ለማየት ግልጽ የሆነ ቦታ ልክ እንደ ፍሪጅ ወይንም የቀን መቁጠሪያችሁ ላይ ለጥፉት ። ለቀጣይ ሰላሳ ቀናትም እቃው ለናንተ አስፈላጊ መሆኑን አስቡበት። ከሰላሳዎቹ ቀናት በኋላም በአስፈላጊነቱ የምታምኑበት ከሆነ ሂዱና ግዙት። ይሄው መንገድ የነገሮችን አስፈላጊነት እንድናስብበት ዕድል ከመስጠቱም ባለፈ በችኮላና ባለማስተዋል ከምናወጣው ወጪ እንድንቆጠብ የሚያደርግ በጣም ውጤታማ መንገድ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ልክ እንዳየናቸው በጣም አስፈላጊ መስለውን ከገዛናቸው በኋላ ግን ያን ያህል ያልወደድናቸውና ያልጠቀምንባቸው እቃዎች እና ለነሱ የምናወጣውን ገንዘብ በከንቱ ከማባከን ይጠብቀናል።
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚያስቡት ወጪን መቀነስ ብቻ ነው። ወጪን መቀነስ ጥሩ አማራጭ ቢሆንም ከዚህ ባለፈ ተጨማሪ ገቢን ማመንጨት ደግሞ ከሁሉ ላቅ ያለ አካሄድ ነው። በስራ ቦታችሁ ደሞዝ ለማስጨመር ሞክሩ ፣ አመቺ ጊዜ ካለም ሁለተኛ ስራ ስሩ ወይንም አልፎ አልፎ መሰራት የሚችሉ ፕሮጀክቶችና ተባራሪ ስራዎች ለመስራት ሞክሩ። እናንተ ያላችሁን ክህሎት በመጠቀም ገቢ የሚያስገኝላችሁን ስራ ስሩ። ከዚህ የምታገኙትን ተጨማሪ ገንዘብም በመቆጠብ የቁጠባ ሂሳባችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያድግ ታያላችሁ። ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሱስ ያሉ መጥፎ ልምዶችን ለመተው ሞክሩ። መጥፎ ልማዶች ከምታስቡት በላይ ገነዘብን ጨራሾች ናቸው። ለአንዳንድ ሰዎች ማጨስ ፣ መቃም፣ መጠጣት፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምና ከልክ በላይ መመገብን ማቆም ቀላል አይደለም። ነገር ግን እንዚህንና መሰል መጥፎ ልማዶችን ማቆም ጤንነታችሁ እንዲጠበቅ እና ገንዘባችሁም እንዲቆጠብ ይረዳችኋል።
ገንዘብን መቆጠብ እንደምታስቡት በጣም የተወሳሰበ እና አስቸጋሪ ነገር አይደለም። ትንንሽ የሚመስሉ ለውጦችን በማድረግ ብዙ ገንዘብ ማቆጠብ ይቻላል። ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ይህንን በምታደርጉበት ጊዜ የገንዘብን ዋጋ ከመረዳት አልፋችሁ በራሳችሁ ገንዘብን ለመቆጠብ የሚያስችሏችሁን ዘዴዎች መቀየስ ትችላላችሁ። ይህም ድንገተኛ ወጪዎች በሚገጥሟችሁ ጊዜ ሳትጨንናነቁ ማውጣት እንድትችሉ ይረዳችኋል። ከዚህም ባለፈ ሁሌም ተጨማሪ ገንዘብ ካላችሁ ደህነንት እንዲሰማችሁ እና ለነገ እንዳትሰጉ ያግዛችኋል።
አሁን ባቀረብንላችሁ መንገዶች ምን ሀሳብ አላችሁ? ከነዚህ ሀሳቦች በተጨማሪ ሌሎች ምን አይነት መንገዶችን ብንጠቀም ገንዘባችንን መቆጠብ እንችላለን ብላችሁ ታስባላችሁ? የናንተ የግል የቁጣብ ባህል ምን አይነት ነው? ልምዳችሁን፣ ሀሳብና አስተያየታችሁን በመልዕክት መስጫው ስር አስቀምጡልን። እስካሁን ስለተከታተላችሁን እናመሰግናለን።